በሕገ-ወጥ መንገድ የተያዘ 460 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ለአርሶ አደሮች ተላለፈ

66

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ ግለሰብ በሕገ-ወጥ መንገድ ለዓመታት ይዞት የነበረውን 460 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ለአርሶ አደሮች አስተላለፈ።

በቀጣይም በከተማዋ ውስጥ ጾሙን የሚያድር መሬት እንደማይኖር ተገልጿል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ጀሞ መድሃኒያለም በተባለው አካባቢ አንድ ግለሰብ አርሶ አደሮችን በማታለል በህገ ወጥ መንገድ ያጠረውን መሬት ማስመለሱን ከአንድ ወር በፊት ከተማ አስተዳደሩ አስታውቆ ነበር።

በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ 460 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት በስፍራው ነባር ለተባሉ ከ160 በላይ አርሶ አደሮች አስተላልፈዋል።

ምክትል ከንቲባው በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መሬቱ በግለሰብ እጅ ታጥሮ በግለሰቡም ሆነ በአርሶ አደሮች ሳይለማ ለዓመታት ሳይለማ ቆይቷል፤ አርሶ አደሮችና ልጆቻቸውም ጾም አድረዋል።

ከዚህ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ታጥረው የተቀመጡ መሬቶች በሙሉ ተነጥቀው ለከተማ ግብርና እና ለሌሎች የልማት ስራዎች እንደሚውሉ ገልጸዋል።

አሁን ለአርሶ አደሮች የተላለፈው መሬትም የከተማ ግብርና ልማት እንደሚካሄድበት ተናግረዋል።

ለአርሶ አደሮች ባስተላለፉት መልዕክት "የሁሉም ማዕከል በተለይ የኦሮሞ ትግል ማዕከል አዲስ አበባና አዲስ አበባ ነው" ያሉት ኢንጂነር ታከለ፤ አርሶ አደሩ መሬቱን ለማይገባ ነገር አሳልፎ እንዳይሰጥ አሳስበዋል።

በከተማው የነበረውን የመሬት መቀራመት ድርጊት አርሶ አደሩ ቢረሳው እንኳን ታሪክ እንደማይረሳው አስታውሰዋል።

በቀጣይም ሳይለማ ታጥሮ የሚቀመጥ መሬት እንደማይኖር አረጋግጠዋል።

መሬቱ የተላለፈላቸው ነባር አርሶ አደሮችም ጾም ሲያድር የነበረውን መሬት እርስ በርሳቸው ተስማምተው በከተማ ግብርና በማልማት ለከተማዋ ምርታቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ አርሶ አደሮቹ ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን የእርሻ ግብዓት እንደሚያቀርብ አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ፈትያ መሃመድ በበኩላቸው በከተማዋ ዙሪያ በልማት ስም የአርሶ አደር መሬት እየታጠረ ሲያዝ መቆየቱን ገልጸዋል።

''በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት በዚህ ወቅት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግና የከተማውን የምግብ አቅርቦት ፍላጎት ለማሟላት በህገ-ወጥ መንገድ ታጥረው የተቀመጡ መሬቶች ለከተማ ግብርና ልማት ይውላሉ'' ብለዋል።

ለዚህም ተቋማቸው ትራክተርን ጨምሮ የተለያዩ የእርሻ ስራ ግብዓቶችን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

መሬት ከተላለፈላቸው ነባር አርሶ አደሮች መካከል ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ግሰለቡ መሬታቸውን በማታለል ወስዶባቸው እንደነበር ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ መሬቱን እንዲያለሙ ስለመለሰላቸውም አመስግነዋል።

ከአንድ ወር በፊት ሚያዚያ 17 ቀን 2012 ዓ.ም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከ460 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የመንግስትና የህዝብን መሬት ያለአግባብ አጥረው የተገኙ ግለሰቦችን ጉዳይ እያጣራ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።

በዚህም አንድ ግለሰብ ብቻ በህገ-ወጥ መንገድ 60 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን በምርመራ ማረጋገጡን ገልጾ፤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በተለምዶ መስታወት ፋብሪካ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ ግለሰብ የአርሶ አደሮችን፣ ለተቋማት ተከልለው የተቀመጡ እና በመሬት ባንክ የሚገኙ በጥቅሉ 460 ሺህ ካሬ ሜትር ወይም 46 ሄክታር መሬት በህገ-ወጥ መንገድ አጥሮ ማስቀመጡን አታውቆ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም