በደቡብ ክልል ህግ የተላለፉ 7 ሺህ አሽከርካሪዎች ተቀጡ

79

ሐዋሳ፣  ግንቦት 17/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የወጡ ክልከላዎችን የተላለፉ 7 ሺህ አሽከርካሪዎች መቀጣታቸውን የክልሉ ምከትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለፁ ።

 ለህዝቡ ደህንነትና ስጋት የሚፈጥሩ አካላት ላይ መንግሥት ጠበቅ ያለ ህግ የማስከበር እርምጃ እንደሚወስድም  ገልጸዋል።

አቶ ርስቱ በመግለጫቸው እንዳመለከቱት ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የወጣውን አዋጅና ክልከላዎችን ጥሰው የተገኙ አሽከርካሪዎች እንዲቀጡ ተደርጓል።

የፊት መሸፈኛ ጭምብል ባለማድረግ ፣ከተፈቀደላቸው የሰው ቁጥር በላይ በማሳፈርና ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ በመያዛቸው ቅጣት ተላልፏባቸዋል ብለዋል።

ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከማስተማር ስራ ጎን ለጎን በአሽከርካሪዎች ላይ በተወሰደው ህግ የማስከበር ርምጃ 8 ሚሊዮን ብር ተቀጥተዋል ።

"ህዝብን በመልካምነት ማገልገል ዋጋው ከገንዘብ በላይ ነው "ያሉት አቶ ርስቱ ህግ የማስከበር ስራው የተሳፋሪዎችን ብቻ ሳይሆን የረዳትና የሹፌሮችን ህይወት ለመታደግ ጭምር ነው ብለዋል።

ትራፊክ አየኝ አላየኝ ሳይሉ የፊት መሸፈኛ ጭንብል በመጠቀም ለህይወታቸው ደህንነት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ግማሽ ተሳፋሪ ከጫኑ ክፍያው እጥፍ እንዲሆን ህግ መውጣቱን ጠቅሰው በተለይ አዋሳኝ ከሆነው ኦሮሚያ ክልል ጋር የተጣጣመ ህግ መውጣቱን አውስተዋል።

ህግን ከማክበር ረገድ መሰላቸት አያስፈልግም ያሉት አቶ ርስቱ ትናንት አደረኩት ብለን ዛሬ ሳናደርግ የምናልፋቸው የጥንቃቄ ጉድለቶች ለኮሮና ቫይረስ ሊያጋልጡን እንደሚችሉ ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አብራርተዋል።

መናኸሪያ አካባቢ በትራንስፖርት ማህበራትና በመንግስት ድጋፍ የተሳፋሪዎችንና የተሽከርካሪዎችን ንጽህና ለመጠበቅ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ለወረርሽኙ መፍትሄ እሰከሚመጣ ድረስ ጥንቃቄ ማድረጉንና ህግን ለማስከበር የሚወሰደውም ርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል።

ለህዝቡ ደህንነትና ስጋት የሚፈጥሩ አካላት ላይ መንግሥት ጠበቅ ያለ ህግ የማስከበር እርምጃ እንደሚወስድም  ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በተለይ በከተሞች አካባቢ ሥርቆት እየተበራከተ መምጣቱን ገልፀው፤ ይህንኑ ተከትሎ የክልሉ ነዋሪዎች መንግስት የታሰሩ ሰዎችን በገፍ ለቆብን ደህንነታችን ችግር ውስጥ ገባ ብለው ቅሬታ ማቅረባቸው ተገቢ አለመሆኑን  ጠቁመዋል።

መንግስት እስረኞችን በይቅርታ የለቀቀው ወረርሽኙ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ቢከሰት ብዙ ሰው ሊጎዳ ይችላል በሚል መልካም እሳቤ መሆኑን አመልክተዋል።

ዜጎች ከጥፋታቸው ተምረው ሰርተው እንዲለወጡና በምርት ተግባር ላይ በመሳተፍ ለቤተሰቦቻቸውና ለወገኖቻቸው እንደዲተርፉ በማሰብ ይቅርታ መደረጉን አስረድተዋል።

ነገር ግን ይህን የተሰጣቸውን እድል መጠቀም ተስኗቸው የጥፋትን መንገድ በሚከተሉት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።

ጥፋት ሲፈጽም የተገኘ በይቅርታ የተለቀቀበትን ጊዜ እንዲጨርስና በፈጸመው ወንጀልም በድጋሜ ተጠያቂ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።

ለህዝቡ ደህንነትና ስጋት በሚፈጥሩ አካላት ላይ የሚወሰደው ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በየደረጃው የሚገኘው የፀጥታ መዋቅሩም ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በመያዝ የተጣለበትን ተልዕኮ እንዲወጣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም