በገላና ወረዳ በጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብ ድጋፍ ተደረገ

90

ዲላ ፣ ግንቦት 17/2012 (ኢዜአ) የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ በጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ከ63 ሺህ በላይ ሰዎች 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ።

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሮባ ዳንብ እንደገለፁት ድጋፉ በጎርፍ አደጋው የተፈናቀሉ ዜጎች ለችግር እንዳይጋለጡ በማሰብ የተደረገ ነው ።

ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ድጋፍ 105 ኩንታል የጤፍ ዱቄትን ጨምሮ ምስር ፣ ሩዝ ፣ ዘይት ፣ ሽሮና በርበሬን ያካተተ ሲሆን 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል ።

የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ ዩኒቨርሲቲው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በወረዳው ካለፈው ወር መጨረሻ ጀምሮ በተከታታይ የጣለው ዝናብ በፈጠረው ጎርፍ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን የሚናገሩት ደግሞ የምዕራብ ጉጂ ዞን የአደጋ ስጋትና አመራር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገዳ ጎዳና ናቸው።

በአደጋውም የሁለት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በ17 ቀበሌዎች የሚገኙ 63 ሺህ 601 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በ7ሺህ 018 ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ በቆሎ ፣ ቦሎቄ ፣ ጤፍና ቡና እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የዞኑ መንግስት ከአጋር ድርጅቶች ጋር ባደረገው ጥረት 7 ሺህ  የቤት ክዳን መሸፈኛ ፕላስቲክና 3 ሺህ ብርድ ልብስ መሰራጨቱን ጠቁመዋል።

ችግሩ ከዞኑ አቅም በላይ በመሆኑ ለክልል በቀረበው ጥያቄ መሰረትም 800 ኩንታል በቆሎ በመሰራጭት ላይ መሆኑን ሃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ያደረገው ድጋፍ የእለት ጉርስ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በአካባቢው ውሃ ወለድና የወባ በሽታ እንዳይቀሰቀስ እንዲሁም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል ጊዜያዊ የጤና ማዕከል በማቋቋም የቅርብ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የጎረፍ አደጋው ከሌሊቱ 7 ሰዓት ገደማ ድንገት በተኙበት መከሰቱን ተከትሎ ምንም አይነት ንብረት ሳያድኑ ቤትና ንብረታቸውን ላይ ጉዳት ማድረሱን የሚናገሩት በወረዳው የአደጋው ሰለባ የሆኑት ወይዘሮ ሃና ገሮ ናቸው።

ጉዳቱ በቤት ሳያበቃ በአምስት ሄክተር ማሳቸው ላይ የነበረውን በቆሎ ፣ ቦሎቄና ሌሎች ሰብሎች ማውደሙንም ተናግረዋል።

መንግስት ከሚያደርገው ሰብዓዊ ድጋፍ ጎን ለጎን በዘላቂነት እንዲቋቋሙና ዳግም የጎርፍ አደጋው እንዳይከሰት የጎርፍ መውረጃ ቦዮችን መስራትና መሰል የጥንቃቄ ስራዎችን እንዲከናወን ጠይቀዋል።

ሌላኛው የአደጋው ተጠቂ አርሶ አደር ሃላኬ ሱሉዳ በበኩለቸው የጎረፍ አደጋው ከደረሰበት ግንቦት 5 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ ከ10 ቤተሰቦቻቸው ጋር ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ መውደሙን ተከትሎም መንግስት በሚያደርግላቸው ድጋፍ ሕይወታቸውን እየመሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም