በኦሮሚያ ክልል ባለሃብቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች በክልሉ ሁለት ወረዳዎች የሚገኙ የችግኝ ጣቢያዎችን ጎበኙ

69

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17/2012 ( ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ባለሃብቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች በክልሉ ሁለት ወረዳዎች የሚገኙ የችግኝ ጣቢያዎችን ዛሬ ጎበኙ።

ባለሃብቶቹና ፖለቲከኞቹ በክልሉ ምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ እና አዳማ ወረዳዎች የሚገኙ የችግኝ ጣቢያዎች የሚሰሩትን ስራዎች ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ተሳትፈዋል።

በዱግዳ ወረዳ በ2 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ በሚያዘጋጀው ፍሎራዜ ችግኝ ጣቢያ ተገኝተው እየተካሄደ ያለውን ልማት ጎብኝተዋል።

በተመሳሳይ በአዳማ ወረዳ ሶደሬ አቅራቢያ የሚገኝ የአቮካዶ ችግኝ ጣቢያ ጎብኝተዋል።

በጣቢያው ተደራጅተው የሚሰሩ ወጣቶች በአሁኑ ወቅት 45 ሺህ የአቦካዶ ተክል ችግኝ አዘጋጅተዋል።

ይህ ችግኝ ለገበያ በሚውልበት ወቅት ሶስት ሚሊዮን ብር ገቢ ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

በክልሉ በሚገኙ ሌሎች ዞኖችም በተመሳሳይ ተደራጅተው በችግኝ ማልማት ስራ ላይ የተሰማሩ በርካታ ወጣቶች መኖራቸው ተጠቁሟል።

በጉብኝቱ ከተሳተፉት ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አባቢያ አባጆቢር ''በግብርና ልማት የተሰራው ስራ ያኮራል'' ብለዋል።

ባለሃብቶች በክልሉ የግብርና ልማት ስራ ቢሰማሩ የሚያዋጣቸው መሆኑን በመግለጽ የጥሪ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ባለሃብቱ አቶ ገምሹ በየነ በበኩላቸው በግብርና ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ባለሃብቶቹና ፖለቲከኞቹ ዛሬ ማለዳ በምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ መቂ ከተማ አቅራቢያ በ 2 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ የሚገኝ የፓፓያ ክላስተር ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት ፖለቲከኛው አቶ ሌንጮ ለታ በአካባቢው እየተካሄደ ያለው የግብርና ልማት ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች መስፋፋት እንዳለበትም አመልክተዋል።

የክልሉ እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በፓፓያ ልማት ላይ የተሰማሩት አርሶ አደሮች በማህበር ተደራጅተው በአዲስ አበባ ምርታቸውን ለመሸጥ የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም