በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን በኩታ ገጠም የቢራ ገብስ ልማት እየተካሔደ ነው

122

ፍቼ፣ ግንቦት 17/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በኩታ ገጠም የእርሻ ዘዴ በመጠቀም የተጀመረው የቢራ ገብስ በመስኖ የማልማት ስራ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማሳየቱን የክልሉ የስራ ኃላፊዎችና አርሶ አደሮች ገለፁ ።

ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ በጂዳ ወረዳ በኩታ ገጠም የመስኖ እርሻ በቢራ ገብስ የተሸፈነው መሬት ተስፋ ሰጪ ውጤት በማሳየቱ በርካታ የክልሉ የስራ ኃላፊዎችና አርሶ አደሮች ልምድ እንዲቀስሙበት ተደርጓል ።


በልማቱ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል የሲበ ሲርጢ ቀበሌ ነዋሪ ደረጀ ዋቄ በሰጡት አስተያየት ለበርካታ አመታት ከሳር ውጪ ምርት የማይሰጥ የነበረው መሬት በባለሙያዎች ምክር በመታገዝ በበጋ ወራት ወንዞችን በመጥለፍ በኩታ ገጠም የመስኖ እርሻ የቢራ ገብስ ማምረት መጀመራቸውን ተናግረዋል ፡፡


በዚህም ባለፈው ዓመት በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ያለሙት 8ዐ ኩንታል የቢራ ገብስ ምርት ተጠቃሚ ስላደረጋቸው ዘንድሮ አጠናክረው እንደቀጠሉበት ተናግረዋል ።

ምርታማ ያደረጋቸውን  መልካም ልምድ ለአካባቢውና ለክልሉ አርሶ አደሮች በማካፈል በርካታ ተከታዮችን በማፍራት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል ።

ሌላው የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ደንደና ኢረና በበኩላቸው  መሬታቸው ለመስኖ እርሻ ተስማሚ መሆኑን ሳያውቁ ለዓመታት መቆየታቸው እንደሚቆጫቸው ጠቁመው አሁን ባገኙት ግንዛቤ ወደ ልማት በመግባት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል ።

ባለፈው ዓመት በኩታ ገጠም የመስኖ ልማት ከሁለት ሄክታር መሬት የቢራ ገብስ ሽያጭ አንድ መቶ ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ጠቁመው ለበለጠ ልማት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል ።

ከመስኖ ልማቱ በሄክታር ከ40 እስከ 50 ኩንታል የቢራ ገብስ ማምረት በመቻላቸው ሌሎች አርሶ አደሮች አርአያነታቸውን እንዲከተሉ ልምድ በማካፈል ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

ሌላው አርሶ አደር ተስፋዬ ጁፋር እንዳሉት በበጋ ወራት ውሃን በማሰባሰብ በኩታ ገጠም የመስኖ እርሻ የሚያመርቱት የቢራ ገብስ በገበያ ተፈላጊ መሆኑ በመረዳታቸው ዘንድሮ በአንድ ሄክታር መሬታቸው ላይ ልማቱን እያከናወኑ ይገኛሉ ።

የጅዳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደረጀ ታደሰ እንደገለፁት በወረዳው በሙከራ ደረጃ 70 በሚጠጉ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ላለፉት ሶስት አመታት የተካሄደው የኩታ ገጠም የመስኖ እርሻ ውጤታማ ሆኗል ።

ይህንኑን ተከትሎ በሁለት ወራት ውስጥ 3ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች፣ የክልልና የፌዴራል የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የግብርና ባለሙያዎች የአርሶ አደሮቹን ማሣ በመጐብኘት ጥሩ ልምድ መቅሰማቸውን ተናግረዋል፡፡ 

በቅርቡም በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የተመራ የልኡካን ቡድን በአርሶ አደሮቹ ማሣ በመገኘት ያዩትን ተሞክሮ ወደ ሌሎች የክልሉ አርሶ አደሮች እንዲስፋፋ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን አስታውሰዋል።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹም ከወረዳው አርሶ አደሮች የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ ለማስፋፋት የሚያስችል እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል ።

በኦሮሚያ ክልል ቢራ ፋብሪካዎች የሚፈልጉትን የጥራት ደረጃ ያሟላ የቢራ ገብስ በሄክታር ከ40 እስከ 5ዐ ኩንታል ማምረት እንደሚቻል አርሶ አደሮቹ በተግባር ማረጋገጣቸውን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም