የኮቪድ 19 ወረርሽ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደረሷል... ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

129

ግንቦት 17/2012(ኢዜአ) ከጊዜ ወደ ጊዜ የኮቪድ 19 ወረርሽ ስርጭት አሳሳቢ በሆነ ደረጃ እየተስፋፋ በመምጣቱ የችግሩን አስከፊነት ከግምት ያስገባ የጥንቃቄ እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡

የሚኒስትሮች ኮሚቴ ከኮቪድ-19 አማካሪ ግብረ-ሃይል ጋር በወቅታዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት እና መከላከል ዙሪያ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የተደገፈ ውይይት አካሄደዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን፤ የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ እና አሳሳቢነቱ እየጨመረ በመምጣቱ የፀረ-ኮቪድ 19 እንቅስቃሴ በትኩረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

የኮቪድ-19 አማካሪ ግብረ-ሃይል አባላት በበኩላቸው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚስተዋለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት በቁጥር እና በፍጥነት አዝማሚያው እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመላው ሃገሪቱ ከተመረመሩት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ከአዲስ አበባ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ በመዲናዋ ማህበረሰብ ዘንድ ወረርሽኙ በአሳሳቢ ደረጃ ስርጭቱ እየጨመረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ከመዲናዋ በርቀት እና በቅርበት በሚገኙ አከባቢዎች ጭምር አሳሳቢ ነው ያሉት አቶ ደመቀ፤ ህብረተሰቡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሳይዘናጋ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

መላው ህብረተሰብ የወረርሽኙን ስርጭት አሳሳቢነት በመገንዘብ እጅን በየጊዜው በመታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን ጠብቆ በመንቀሳቀስ እና የፊት ማስክ በመጠቀም እንዲከላከል ጥሪ መቅረቡን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

ከኮቪድ-19 አማካሪ ግብረ-ሃይል ሙያዊ ማብራሪያ ተከትሎ፤ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የኮቪድ-19 የምርመራ ስራው እንዲጠናከር፣ ችግሩን የሚመጥን የህግ ማስከበር ስራ ተግባራዊ እንዲደረግ፤ እንዲሁም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስልጠና ተሰጥቷቸው ህብረተሰቡን የማስተማር ስራ ላይ እንዲሰማሩ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም