በአማራ ክልል 90 ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት ወደ መኽር እርሻው እንዲገባ ይደረጋል

94

ባህር ዳር፣ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በአማራ ክልል በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የግብርና ምርታማነት እንዳይቀንስ 90 ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት ወደ ልማት ለማስገባት ልየታ መካሄዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።


የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ ለኢዜአ እንደገለፁት አርሶ አደሩ እራሱን ከኮሮና በመጠበቅ የግብርና እርሻ ስራውን እንዲያጠናክር ድጋፍ እየተደረገ ነው።

በክልሉ በየዓመቱ ከአራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመኽር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች እንደሚለማ አስታውሰዋል።

ባለፈው ዓመት በሰብል ዘር ከተሸፈነው መሬትም 106 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰው፤ በዘንድሮው የመኽር አዝመራ 127 ሚሊዮን ኩንታል እህል ለማምረት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

እስካሁን በተደረገ ጥረትም ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱንና አንዳንድ አካባቢዎችም በቆሎና ገብስ መዘራት መጀመሩን ተናግረዋል።

በክልሉ ከኮሮና መከሰት ጋር ተያይዞ የምርት መቀነስ እንዳይከሰት ከዚህ በፊት በተቋማት፣ በግለሰቦችና በባለሃብቶች እጅ የነበረና ከምርት ውጭ ሆኖ የቆየ 90 ሺህ ሄክታር መሬት ወደ ልማት ለማስገባት ተለይቷል።

መሬቱ ወደ ልማት የሚገባውም በበሽታው ምክንያት የምርት መቀነስ እንዳይከሰትና ከዚህ ጋር በተያያዘ ረሃብ እንዳይከሰት ለመከላከል በማቀድ ነው።

መጀመሪያ የመሬቱ ባለቤቶች እንዲያለሙት እድል ይሰጣል ያሉት ኃላፊው ፤ ማልማት የማይችሉ ከሆነ ደግሞ ለተደራጁና አቅም ላላቸው አልሚዎች በጊዜያዊነት ይተላለፋል።

በዚህ የመኽር ወቅትም አርሶ አደሩ በሽታውን ለመከላከል የቤተሰብ ጉልበትን  በመጠቀምና ረጅም ሰዓት በመስራት ለማካካስ ጥረት ይደረጋል ።

እንደ ምክትል ሃላፊው ማብራሪያ በዚህ ዓመት 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተሰራ ሲሆን እስካሁንም 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታሉ ቀርቦ እየተሰራጨ ይገኛል።

ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ማጋጠሙን ጠቅሰው፤ ለመኽር እርሻው 243 ሺህ ኩንታል የሰብል ምርጥ ዘር ቢያስፈልግም በሚፈለገው ልክ አልቀረበም ።

እስካሁን ድረስ 90 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ብቻ መቅረቡን ገልፀው፤ አርሶ አደሩ የተሻሉ ዘሮችን በመዋዋስ እንዲጠቀም እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ።

በክልሉ በቀጣዩ ዓመት በኮሮና በሽታ ምክንያት የሰብል ምርት የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም እንዳይፈጠር ከወዲሁ በግብርናው ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በድሉ ድንገቱ ናቸው ።

ከዚህ በፊት በተለያየ መንገድ ወደ ሰብል ልማት ያልገባ መሬት በዚህ ዓመት እንዲገባ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ ተግባር ተግብቷል ብለዋል።

ህብረተሰቡን ከኮሮና በሽታ ከመከላከል ጎን ለጎን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅኖ እንዳይፈጠር የተለያዩ ተግባራት ታቅደው እየተተገበሩ ይገኛል ብለዋል ።

በተለያዩ የኢንቨስትመንትና ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ አካላትም የያዙትን የሰው ሃይል ይዘው እንዲዘልቁ የተለያዩ ማበረታቻዎች እየተደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

የበሽታውን አጠቃላይ ሁኔታ በመገምገም ዘላቂ የመፍትሄ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል።

ወቅቱን ጠብቆ እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም የእርሻ ስራቸውን በማካሄድ ላይ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የወራሚት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፈንታሁን መራ ናቸው።

ለመኽር ልማቱ የሚውል ማዳበሪያ በከፊል ማግኘት ቢችሉም የበቆሎ ዘር በማጣታቸው መቸገራቸውን ተናግረዋል።

ከበሽታው ጋር በተያያዘም የእርሻ ስራ የሚያከናውኑ ሰራተኞችን መቅጠር እንዳልቻሉ ገልፀው፤ የቤተሰባቸውን ጉልበት ተጠቅመው እያረሱ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሹመት ላቀ በበኩላቸው የዚህ ዓመት የመኽር እርሻ ቀደም ብለው መጀመራቸውን ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም