በትራንስፖርት አጠቃቀም ላይ የሚታየው መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል - የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ

105

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኅብረተሰቡ በትራንስፖርት እንቅስቃሴው ላይ የሚያሳየው መዘናጋት ለኮቪድ-19 በማጋለጥ ዋጋ እንደሚያስከፍል በዳሰሳ ጥናት አረጋግጫለሁ አለ።

ቢሮው በመዲናዋ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ ታይቶባቸዋል በተባሉት የልደታና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየሰጠ ነው።

አርቲስቶችና ታዋቂ ሰዎች በአካባቢዎቹ ተገኝተው ህዝቡ አካላዊ ርቀቱን እንዲጠብቅ፣ በህዝብ ትራንስፖርት ከመሳፈሩ በፊት የእጅ ንፅህና መጠበቂያ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲጠቀም እያስገነዘቡ ነው።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ስጦታው አካሉ በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች የተደረገው የዳሰሳ ጥናት በትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ተጠጋግቶ መሰለፍ፣ የአፍና የአፍጫ መሸፈኛ አለመጠቀም፣ በወንበር ከአንድ ሰው በላይ መጫን መስተዋሉን ገልጸዋል።

ይህ አይነቱ ጥንቃቄ የጎደለው እንቅስቃሴ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በማስፋፋት ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል ነው ያሉት።

ከጤና ሚኒስቴር የሚወጣው መረጃ እንዳሳየው በቫይረሱ የተያዙ አብዛኞቹ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪና የውጪ አገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው እንደሆኑ አስታውሰዋል።

ይህ የሚያሳየው  ህብረተሰቡ ለበሽታው ትኩረት አለመስጠቱንና ከጤና ባለሙያዎችና ከመንግስት የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦችን በትክክል አለመተግበሩን እንደሆነ ተናግረዋል።   

ህብረተሰቡ ይህን አስቸጋሪ ወቅት የመንግስትን መመሪያዎችና በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫዎች በትክክል በመተግበር ራሱንና ሌሎችንም ከበሽታው መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።  

ቢሯቸው የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ ህዝቡ ለትራንስፖርት ተራርቆ እንዲሰለፍ፣ አገልግሎት ሰጪዎች በወንበር ብቻ እንዲጭኑ የማድረግና ሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎችን ቢተገብርም የህብረተሰቡ መዘናጋት የሚፈለገው  ውጤት እንዳይገኝ ማድረጉን አውስተዋል።

የቢሮ ኃላፊው ግንዛቤ በማስጨበጥ ተግባር እየተሳተፉ ያሉ ታዋቂ ሰዎች፣ አርቲስቶችና ሌሎች ድጋፍ እያደረጉ ያሉ ተቋማትን አመስግነው ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ዛሬ በልደታና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች የተጀመረው  የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር በመዲናዋ ሁሉም አካባቢዎች እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አበረ አዳሙ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ሳይኖራቸው በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር የህብረተሰቡን መዘናጋት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

አሁንም ዜጎች ህይወታቸውን ለማትረፍ በመንግስት የሚወጡ አዋጆችና መመሪያዎችን እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን ምክረ ሃሳብ በአግባቡ እንዲተገብሩ መክረዋል።

ዜጎች ራሳቸውን ለማጥፋት ከሚመስል ተግባራቸው ተቆጥበው ራሳቸውንና ወገናቸውን ከበሸታው መታደግ አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም