በመላው ዓለም የኢድ አል ፈጥር በዓል እየተከበረ ነው

159

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2012 (ኢዜአ) በመላው ዓለም በሚገኙ ሙስሊሞች 1ሺህ 441ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል በማክበር ላይ ናቸው።

የቅዱስ የረመዳን ወር ማብቃትን ተከትሎ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሙስሊሞች የኢድ አል ፈጥር በዓል በዛሬው ዕለት እያከበሩ ነው።

በዓሉ አለም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሰዎች እንቅስቃሴ በተገደበበት ወቅት መከበሩ ከሌላው ጊዜ የተለየ አድርጎታል።

በብዛት ሙስሊም ሕዝብ የሚኖርባቸው እንደ ቱርክ፣ ኳታርና ኢንዶኔዥያ ያሉ አገሮች የጠዋት ፀሎትን ጨምሮ አብዛኛዎቹን የኢድ-ተያያዥ እንቅስቃሴ ማገዳቸውን አልጀዚራ በዘገባው አስነብቧል።

የሙስሊም ድርጅቶችና ግለሰቦች የኢድ ባህልን ለማቆየት የቴክኖሎጂና የበይነ መረብ [ኢንተርኔት]አማራጮችን በመጠቀም ላይ ናቸው።

በዓሉን ለማድመቅ እንደ ማህበራዊ ሚዲያንና በኢንተርኔት በቀጥታ የሚተላለፉ ኮንሰርቶች በማሳየት ላይ እንደሚገኙም በዘገባው ተጠቅሷል።

እንደ ሰሜንና ላቲን አሜሪካ ያሉ ዝቅተኛ የሙስሊም ማህበረሰብ የሚገኝባቸው አገሮች ደግሞ በቤት ውስጥ በመሆንና ተዛማጅ ገደቦችን በመተግበር በዓሉን በማክበር ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።

የአሜሪካ-እስላማዊ ግንኙነት ምክር ቤት (CAIR)ና የአሜሪካ-ሲቪል መብቶች ቡድን የአሜሪካ ሙስሊሞች በዓሉን ኢንተርኔትን በመጠቀም እንዲያከብሩ አሳስቧል።

“ኢድ ኳራንት”  የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ዝግጅት ህዝቡ ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች እንዲልኩም ጠይቋል።

“ምንም እንኳን በአካል ቢራራቁም፤ በዓሉን ሰዎች እንዲያከብሩ ማበረታታት እንፈልጋለን” ሲሉ የምክር ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤድዋርድ ሚቼል ተናግረዋል፡፡

በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ዋና ከተማ አቡዳቢ ከተማ የባህልና ቱሪዝም መሥሪያ ቤት ሰሞኑን በኢንተርኔት ኮንሰርቶችን ማቅረቡ በዘገባው ተጠቅሷል።

ጀርመን ከሦስት ሳምንታት በፊት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የ1 ነጥብ 5 ሜትር አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ሐይማኖታዊ አገልግሎት እንዲጀመር ፈቃድ መስጠቷ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ በበርሊን የሚገኘው ዳር አሳላም መስጅድ የእምነቱ ተከታዮች የሚፈለገውን ያህል ርቀት በመጠበቅ ሐይማኖታዊ ሥርዓቱን ለማካሄድ ላልቻሉ ሙስሊሞች የማርቲን ሉተርን ቤተ-ክርስቲያን በር ከፍታ ፀሎታቸውን እንዲሰግዱ ፈቅዳለች ሲል ቢቢሲ በድረ ገጹ አስነብቧል።

ከዓለም ሕዝብ ሁለት ቢሊዮን ያህሉ ሙስሊም መሆኑንና ከዓለም ሃይማኖት እስልምና ሁለተኛውን ደረጃ መያዙን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም