በቤንሻንጉል ጉሙዝ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሔክታር ለማልማት እንቅስቃሴ ተጀምሯል

106

አሶሳ ፣ ግንቦት 15 / 2012 ዓ.ም. (ኢዜአ)  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘንድሮው የመኸር አዝመራ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ለማልማት እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

በቢሮው የሰብል ልማት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ፍቅሩ አቡኖ እንደተናገሩት በክልሉ በ2012/2013 የመኸር አዝመራ 1 ሚሊዮን 125 ሺህ 712 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል ።

እሰከ አሁን ድረስ  213 ሺህ 188 ሄክታር መሬት ታርሶና ለስልሶ ለዘር ተዘጋጅቷል ፡፡

በእርሻ ስራው የሚሳተፉ አርሶ አደሮች በተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት፣ በኩታ ገጠም እርሻ ዘዴና በበረሃ አንበጣ መከላከል ስልጠና እንደተሰጣቸውም ኃላፊው ተናግረዋል ።

በየደረጃው ከሚገኙ የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ግብረ ሃይሎች ጋር  በመቀናጀት የእርሻ ስራው ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት የጸዳ እንዲሆን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ትኩረት እንደተሰጠው አብራርተዋል፡፡

አርሶ አደሩ በምርት ዘመኑ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ  የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማምረት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችለው ዝግጅት አድርጓል ።

በአርሶ አደሩ ፍላጎት መሠረት ከሚቀርበው 160 ሺህ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ውስጥ ከግማሽ በላይ ተጓጉዞ ለተጠቃሚዎች መድረሱንም አቶ ፍቅሩ ገልፀዋል ።

ክልሉ ከመኽር አዝመራው ከ38 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ።

እየጣለ የሚገኘውን የክረምት ዝናብ ለመጠቀም የማሳ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ በአሶሳ ወረዳ የአምባ ስምንት ቀበሌ አርሶ አደር አቶ አህመድ ዓሊ ናቸው፡፡

ካላቸው አንድ ሄክታር መሬት ግማሽ ያህሉን አርሰው ማለስለሳቸውን ጠቅሰው ማዳበሪያ በግዥ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በእርሻ ስራ ወቅት እርሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚያደርጉት ዋነኛው የጥንቃቄ መንገድ እንደሆነም አርሶ አደሩ ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም