በደቡብ ክልል 134 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ርብርብ እየተደረገ ነው- የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

116

ሐዋሳ (ኢዜአ) ግንቦት15/2012 በደቡብ ክልል ከመኽር አዝመራው 134 ሚሊዮን ኩንታል እህል ለማምረት ታቅዶ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።
በክልሉ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከልም  ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል ።

አርሶ አደሩ ከኮሮና ወረርሽኝ እራሱን በመጠበቅ በምርታማነት ዕድገትና በአካባቢ ጥበቃ ልማት ስራዎች ላይ እንዲተጋም  ጥሪ ቀርቧል።

ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ  ይርዳው በሰጡት መግለጫ ወረርሽኙ ከሚያመጣብን ተፅዕኖ ባልተናነሰ የምርት እድገት መቀዛቀዝ እንዳያጋጥም ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ዘንድሮ በልዩ መንገድ የእርሻ ልማትን ማሳደግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ርስቱ  በተለይ የክልሉ አርሶ አደር ያለውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ ለማልማት መትጋት እንዳለበት አሳስበዋል ።

እንደ መንግስት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን ለዚህ ስኬት እስካሁን ያልታረሰ መሬት ጥቅም ላይ እንዲውል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የግብርና ባለሙያዎች በሚሰጡት ምክር መሰረት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዱ ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሩ በአግባቡ እንዲጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል ።

በምርት ዘመኑ 134 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ለመሰብሰብ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በክልል ደረጃ ግብረ ሃይል ተደራጅቶ እስከ ልማት ጣቢያ ሰራተኞች ድረስ ተናብቦ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም መላው የክልሉ አርሶ አደር በሚደረግለት የቴክኒክ ድጋፍ በመታገዝና  ከወረርሽኙ እራሱን በመጠበቅ በማምረት ስራው ላይ እንዲተጋ አቶ ርስቶ ጥሪ አቅርበዋል።

 በጠቅላይ ሚኒስትሩ አምና የተጀመረውን የደን ልማት እንቅስቃሴ ዘንድሮም ለማስቀጠል በክልሉ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በየአካባቢው የተከላ ቦታ በመምረጥና በጉድጓድ ቁፋሮው  ከወዲሁ አርሶ አደሩ ዝግጁ እንዲሆንም ጠይቀዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችም ህብረተሰቡ ለአካባቢ ጥበቃ ልማት እንዲያንቀሳቅሱት አቶ ርስቱ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም