ለህፃናት አእምሮአዊና አካላዊ ጤንንነት አዮዲን ያለው ጨው መጠቀም ያስፈልጋል

151

መቐለ ግንቦት 15/2012 አዮዲን ያልተጨመረበት ጨው መጠቀም በህጸናት አእምራዊና አካላዊ ጤንነት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ አንድ የዘርፉ ምሁር ገለጹ።

በመቐለ ዩኒቨርስቲ የዓይደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና የስነ ምግብ ተማራማሪ ዶክተር አፈወርቅ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንዳሉት ትግራይን ጨምሮ ተዳፉት የእርሻ መሬት ባላቸው የአገራችን አከባቢዎች  ለም አፈሩን በጎርፍ ታጥቦ ስለሚወሰድ የአዮዲን ንጥረ ነገር ይዘታቸው ዝቅተኛ ነው ።

ህብረተሰቡ አዮዲን የተጨመረበት ጨው እንዲጠቀም ቢመከርም በአጠቃቀም ላይ ያለውን የግንዛቤ እጥረት  ግን ገና አልተቀረፈም ብለዋል ።

በትግራይ ክልል አዮዲን የተጨመረበት  ጨው የስርጭት ሽፋን 93 በመቶ የደረሰ ቢሆንም  የጤና ባለሙያዎች በሚያቀርቡት ምክረ ሃሳብ መሰረት የሚጠቀም ህብረተሰብ ግን ገና ከ18 በመቶ አልዘለለም እንደማይበልጥ ተናግረዋል ።

በአጠቃቀም ላይ በሚታየው ችግር  ምክንያትም በህጸናት አእምራዊ እድገት ውስንነት ከማስከተሉ  በተጨማሪ ለእንቅርት በሽታ ተጋላጭ እያደረጋቸው መሆኑን አስረድተዋል።

 የአዮዲን ጨው በአግባቡ አለመጠቀም ለድንገተኛ ፅንስ መቋረጥም አንዱ ምክንያት መሆኑንም ነው  ዶክተሩ የገለጹት።

ችግሩን ለመቅረፍ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠት እንዳለበትም ምሁሩ አሳስበዋል ።

በትግራይ ክልል ጤና  ቢሮ የአመጋገብ ስርዓት የስራ ሂደት ባለቤት አቶ መንግሽ ባህረስላሴ በበኩላቸው በአጠቃቀም ላይ ያለው ችግር ትክክል መሆኑ ገልፀዋል።

ሀብረተሰቡ ያለው የግንዛቤ ችግር ለመፍታትም በከተማ እና ገጠር ባሉት የጤና ልማት ቡዱኖች አማካይነት የቤት ለቤት ትምህርት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

 አዮዲን የተጨመረበትና  ያልተጨመበት  ጨው  የሚለይ መሳሪያ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች መሰራጨቱንም ገልጸዋል።

 በሬድዮና በቴሌቪዥን ተከታተይ ትምህርት  ለመስጠትም ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አዮዲን የተጨመረበት ጨው ጠቀሜታውም ሆነ አጠቃቀሙ ለይተው እንደማያውቁ የተናገሩት የመቀሌ ነዋሪ ወይዘሮ አበባ ምስጉን ናቸው።

ሌላው የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ሰንደል ዮሀንስ በበኩላቸው ጨው አዮዲን የተጨመረበት መሆኑንና አለመሆኑን ከማጣራት ባለፈ በአጠቃቀሙ ያለው ልዩነት በውል እንደማይገነዘቡት ተናግረዋል።

ጎሮቤቶቻቸውም የምግብ ጨው ሲጠቀሙ የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት ሳይሆን ልማዳዊ መሆኑን ተናግረዋል ።

ባለሙያዎች እንደሚመክሩት ከሆነ ግን አዮዲን ያለው ጨው ወጡ ፈልቶ ከወረደ በኋላ እሳት ሳይነካው ተጨምሮ ጥቅም ላይ እንዲውል ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም