በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት እጥረት ለማካካስ እየተሰራ ነው

69

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2012( ኢዜአ) በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በ2012/13 ምርት ዘመን ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት እጥረት ለማካካስ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አስታወቁ።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ ከሚያሳድርባቸው መስኮች አንዱ የግብርናው ዘርፍ ነው።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሳኒ ረዲ ለኢዜአ እንደገለጹት በወረርሽኙ ምክንያት ሊገጥም የሚችለውን እጥረት ለመከላከል የተለያዩ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።

ባለፈው የምርት ዘመን  በዋና ዋና የአዝርዕት ሰብሎች 379 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን አስታውሰዋል።

ወረርሽኙ በሚያሳድረው ተጽዕኖ በምርት ዘመን ግን ምርቱ የስምንት በመቶ ቅናሽ ሊታይበት እንደሚችል ገልጸዋል።

ይህንን ለመከላከልም1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሔክታር ተጨማሪ መሬት እንደሚታረስ አብራርተዋል።

እጥረቱን ለማካካስም የአግሮ ሜካናይዜሽን የሚሰጡ የኅብረት ሥራ ማህበራትና ሌሎች አካላት ዝግጅት አድርገው አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

የመንግሥትና የግል ሰፋፊ እርሻ ባለቤቶችም የእርሻ መሣሪያዎች ጠግነው በዙሪያቸው ለሚገኙ አርሶ አደሮች ድጋፍ እንዲሰጡ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የሊዝ ፋይናንስ ተቋማትም በእጃቸው ባሉት የእርሻ መሣሪያዎች አገልግሎት የሚሰጡበት መንገድ እየታየ መሆኑን አስረድተዋል።

አሲዳማ መሬት በማከምና ምርታማ እንዲሆኑም በማድረግ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ሥራዎችን ማከናወንም ሌላው አቅጣጫ እንደሆነም አስረድተዋል።

የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በበኩላቸው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የምግብ እጥረት እንዳይከሰት በጋራ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በተለይ የእርሻ ሥራው በሚፈለገው መልኩ እንዲካሄድ አርሶ አደሩ ራሱን ከወረርሽኙ ጠብቆ የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውን የግብርና ባለሙያዎችና የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

እንደ አቶ ምትኩ ገለጻ ቫይረሱ በኢትዮጵያ መኖሩ ከተረጋገጠ ወዲህም የምግብ እጥረት እንዳይገጥም ኮሚሽኑ ዕቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።


በአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ተመራማሪ ፕሮፊሰር በላይ ስምአኒ በበኩላቸው የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥንቃቄዎችን መተግበር አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።

ነገር ግን አርሶ አደሩም ሆነ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ለምግብ እጥረትና ሌሎች ችግሮች ተጋላጭ እንዳይሆኑ መስራት  ይገባቸዋል ብለዋል።

ባለሃብቶች፣መንግስትና ተመራማሪዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ሊደርስ የሚገባውን ተጽእኖ በመቀነስ  አስተዋጽኦና ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም