ኃይለማርያም እና ሮማን የተሰኘ ፋውንዴሽን ሊቋቋም ነው

265
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከባለቤታቸው ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ጋር "ኃይለማርያም እና ሮማን" የተሰኘ ፋውንዴሽን ሊያቋቁሙ ነው። ፋውንዴሽኑ ጥቃት የደረሰባቸውና ሌሎች ድጋፍ የሚፈልጉ ሕጻናትና ሴቶችን መንከባከብ ላይ አተኩሮ ይሰራል ተብሏል። አገር አቀፍ የሴቶች ማረፊያ ማኅበርና የሴቶች ይችላሉ ማኅበር ወደ አመራርነት የመጡ ሴቶችንና ድጋፍ ያደረጉ አካላትን እውቅና ለመስጠት የምስጋና መርኃ ግብር ትላንት በአዲስ አበባ አዘጋጅተዋል። በዚሁ ጊዜ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን "ኃይለማርያም እና ሮማን" የተሰኘ ፋውንዴሽን ሊቋቋም መሆኑን ጠቁመዋል። ፋውንዴሽኑን ለማቋቋም የሚያስፈልጉ የዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቃቸውን የገለጹት ወይዘሮ ሮማን ፋውንዴሽኑ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ ፍንጭ ሰጥተዋል። ፋውንዴሽኑም ድጋፍ የሚሹና ጥቃት የደረሰባቸው ሕጻናትና ሴቶችን በመንከባከብ በአገሪቱ ማህበራዊ ልማት ላይ ጉልህ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል። በተለይም ጊዜው ለሴቶች ልዩ ትኩረት የተሰጠበት ወቅት በመሆኑ በተለያዩ መስክ የተሰማሩ ሴቶችን ድጋፍ ለማድረግና ለማቋቋም መዘጋጀታቸውን ወይዘሮ ሮማን አረጋግጠዋል። የሴቶች ማረፊያ ልማት ማኅበር መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር በበኩላቸው ጊዜው ሴቶች ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሴቶችን ተሷትፏቸውና ውሳኔ ሰጪነታቸው እንዲዳብር ያስቀመጡት አቅጣጫ ትልቅ ግብዓት መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ደግሞ በቀጣይም ሴቶች ባሉበት የሙያ መስክ በአመራርነት ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጎለብቱ ተስፋ ይሰጣል ብለዋል። በመርኃ ግብሩ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ሴቶች፣ አንጋፋ የኪነጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ሴት ባለሙያዎች፣ የሴቶችና ህጻናት መብት ተሟጓች የሕግ ባለሙያ ሴቶች ተገኝተዋል። ጎን ለጎንም በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርተው ድጋፍ የሚሹና የተጠቁ ሴቶችና ሕጻናት የሚያግዙ ሴቶች እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም