ምክር ቤቱ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳለፈ

84

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14/2012 (ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬ ዕለት ባካሄደው 83ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከልና የሕክምና አገልግሎት ለሚሳተፉ ሠራተኞች የማበረታቻ አበል ክፍያ እንዲሰጥ ወስኗል።

ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንደሚያመለክተው ምክር ቤቱ በሰባት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የጂኦተርማል ሀብት ልማት ዓዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ ዓዋጅ ላይ ሲሆን በዓዋጁ በግልጽ ያልተብራሩና አሁን በሚካሄዱ የጂኦተርማል ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ የሚገኙ አሠራሮች እንዲሻሻሉ ማስፈለጉን ተመልክቷል።

በመሆኑም የነባሩን ዓዋጅ የተወሰኑ ድንጋጌዎች ለማሻሻል የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ረቂቅ ዓዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

የኮቪድ19 ወረርሽኝን በመከላከልና የሕክምና አገልግሎት በመስጠት በቀጥታ ለሚሳተፉ የጤና ዘርፍ ሠራተኞች የማበረታቻ አበል ክፍያን ለመወሰን የተዘጋጀው መመሪያ ሌላው ምክር ቤቱ የተመለከተው አጀንዳ ነው፡፡

ሠራተኞቹ ወረርሽኙን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ለማከም በሚደረገው ጥረት በግንባር ቀደምነት በሙያቸው የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ እጅግ የላቀ ከመሆኑም በላይ፤ የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ጤንነትና ሕይወት ለአደጋ በማጋለጥ የሚፈጸም ሙያዊ አስተዋጽዖ መሆኑን አምኖበታል።

ምክር ቤቱ የጤና ሚኒስቴር የማበረታቻ አበል ክፍያን ለመወሰን ባቀረበው ረቂቅ መመሪያ ላይ ከተወያየ በኋላ ተቀብሎ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የፌዴራል መንግሥት የ2012 በጀት ዓመት የተጨማሪ በጀት ረቂቅ ዓዋጅ እንዲሁም የመካከለኛ ዘመን (2013-2017) የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ ላይ ነው፡፡

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በኢኮኖሚው ላይ የተከሰተውን ተጽዕኖ ለመቋቋምና የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ለመሸፈን የ2012 በጀት ዓመት የተጨማሪ በጀት ረቂቅ ዓዋጅ እንዲሁም የመካከለኛ ዘመን (የ2013-2017) የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ውሳኔ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው የተጨማሪ በጀት ረቂቅ ዓዋጅና የመካከለኛ ዘመን (2013-2017) የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ዓዋጁ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ እንዲሁም ማዕቀፉም በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

ምክር ቤቱ በመጨረሻ የተወያየው ለሕዝብ ጥቅም መሬት ሲለቀቅ ስለሚከፈል ካሳና የልማት ተነሺዎችን መልሶ ስለማቋቋም በወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ላይ ነው፡፡

ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትንና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን በዓዋጅ ቁጥር 1161/2011 የወጣውን ዓዋጅ ለመተግበር የቀረበውን  ደንብ ተመልክቷል።

በዓዋጁ ይዞታቸውን የሚለቁ ዜጎች በዘላቂነት የሚቋቋሙበት የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዋስትና እንዲኖራቸው የሚያስችል የካሳና የመልሶ ማቋቋም ሥርዓት የሚዘረጋበት ማስፈጸሚያ ረቂቅ ደንብ  ለምክር ቤቱ ውሳኔ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣና በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም