የኮቪድ -19 ስርጭትን ለመግታት የፈጠራ ባለሙያዎች ምን ሰሩ?

113

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14/2012 (ኢዜአ) የኮቪድ -19ን ስርጭትን ለመግታት የፈጠራ ባለሙያዎች የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች ዘርፈ ብዙ የፈጠራ ሥራዎችን እያበረከቱ ሲሆን በቅርቡም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኮቪድ-19 ላይ ባወጣው የፈጠራ ውድድር ላሸነፉ ባለሙያዎች ትናንት ዕውቅና ተሰጥቷል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የፈጠራ ባለሙያዎች ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰተ ጀምሮ በፈጠራ ሥራ ላይ መሰማራታቸውና ስለፈጠራ ሥራዎቻቸው ተናግረዋል።

ከነዚህ መካከል ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጣው አቶ ሙሉቀን አንተነህ ለገጠርና ከተማ ታካሚዎች የሚሆን ሜካኒካል ቬንትሌተር፣ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ባዮሜዲካል ኢንስቲትዩት የመጣው ሀብታሙ አባፎጌ ጨረርን በመጠቀም ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚያስችል ማሽን አቅርበዋል።

ወጣት ብሩክ ግርማ ከአዲስ አበባ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ከእጅ ንክኪ ነጻ የእጅ ማስታጠቢያ እንዲሁም አቶ ፋኒ ነስር ለሕሙማን በቤታቸው የሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል 'መድኃኒት-ኢቲ' የተሰኘ መተግበሪያ ሰርተዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎቹ በኢትዮጵያ በርካታ የፈጠራ ባለሙያዎች የፈጠራ ሥራዎች እንዳሏቸው ገልጸው፣ ባለሙያዎችን መደገፍ ቢቻል ውጤታማ ሥራ መስራት እንደሚቻል ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የፈጠራ ባለሙያዎች የኮቪድ-19ን ወረርሸኝ የሚያስከትለውን ቀውስ ለመከላከል የፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲጠቀሙና ማህበረሰቡን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ መክብብ ታደሰ በበኩላቸው በዚህ ዓመት ማህበራቸው የተቋቋመበት ዓላማ የፈጠራ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ በተደራጀ ሁኔታ የፈጠራ ሥራዎችን ለመስራት  መሆኑን አመልክተዋል።

ማህበሩ መመስረቱ ለኮቪድ-19 ጥሪ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ጠቁመው፣ የፈጠራ ባለሙያዎች ድጋፍ ማግኘት የሚችሉባቸውን መንገዶች ለማመቻቸትም መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ተናግረዋል።

በዚህም ማህበሩ የፈጠራ ባለሙያዎችን መታገዝ የሚችሉበት መንገድ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም