የኮቪደ-19 ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ 12 የፈጠራ ሥራዎች እውቅና ተሰጣቸው

129

ዲስ አበባ፣ ግንቦት 14/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ 12 የፈጠራ ሥራዎች በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እውቅና ተሰጣቸው።

ፈጠራዎቹ የኮሮናቫይረስ ሕሙማንን ለማከም ከሚያስችሉ ቬንትሌተሮች ጀምሮ የተለያዩ የእጅ መታጠቢያ መሳሪያዎችና መተግበሪያዎች ናቸው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር የኮቪድ-19ን መዛመትን ለመከላከል የሚያችሉ የፈጠራ ሥራዎች ውድድር አካሂዶ ነበር።

በውድድሩ ላሸነፉ 12 የፈጠራ ሥራዎች ትናንት ማምሻውን  የእውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል።

ውድድሩ በዲጂታልና አይሲቲ፣ በፈጠራና ኢኖቬሽን እንዲሁም በጂኦ ስፔሻል ሦስት የውድድር ዘርፎች የተካሄደ ሲሆን ለእነዚህም 446 የፈጠራ ሥራዎች ቀርበው 320ዎቹ ለምዘና መለየታቸው በመርሀ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

ከቀረቡት የፈጠራ ስራዎች መካከልም 43 በመቶ ቀጥታ ወደምርት የሚቀየሩ፣ 31 በመቶ ተጨማሪ ሥራዎች የሚፈልጉ፣ ቀሪዎቹ 26 በመቶዎቹ ደግሞ በሃሳብ ደረጃ ስለመሆናቸው ተጠቁሟል።

በውድድሩ ሂደትም በመጀመሪያው ዙር 10 ሜካኒካለ ቬንትሌተሮች፣ 4 አይነተ ብዙ የእጅ ማስታጠቢያ መሳሪያዎች፣ 12 ሶፍትዌሮችና ሌሎች ፈጠራዎችን ያካተቱ በግለሰብ፣ በኢንተርፕራይዝና በቡድን የቀረቡ በድምሩ 30 የፈጠራ ሥራዎች ተመርጠዋል።

በመጨረሻም 12ቱ የፈጠራ ፕሮጀክቶች ተለይተው ለዕውቅና በቅተዋል።

ከተወዳዳሪዎች መካከል ዶክተር ጊዜአዲስ ላመስግን፣ አቶ ሙሉቀን አንተነህና አቶ ሳሙኤል ይትባረክ  በተለያዩ ሜካኒካል ቬንቲሌተሮች፣ አቶ ፋኒ ናስር፣ አቶ አቤል ኪዳነማርያምና አቶ መላኩ ውብሸት በሶፍት ዌር ወይም በተለያዩ መተግበሪያ ፈጠራዎች ያሸነፉ ናቸው።

እንዲሁም አቶ ለገሰ ተፈራ፣ ኤፍሬም አስፋው፣ አቶ አንተነህ ታዬ፣ አቶ ብሩክ ግርማ፣ አቶ ሃብታሙ ነቅዓጥበብ፣ አቶ ሃብታሙ አባፎጌ የእጅ ማስታጠቢያ ማሽኖች በመፈብረክ እውቅና ተሰጥዋቸዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ የፈጠራ ሥራዎቹ ከኮቪድ-19 ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጡና ለፈጠራ መስፋፋት መነሳሳትን የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።

የፈጠራ ሥራዎች ከፕሮጀክት ወደ ውጤት ተለውጠው ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ሚኒስትሩ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

ለቀጣይ አገራዊ ልማትና እድገት የፈጠራ ሥራዎች ወሳኝ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ሥራዎቹ ለገበያ እንዲቀርቡ ለማድረግ የሁሉም ወገን ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ለዚህም የግል ዘርፍ ተዋናዮችና ተቋማት ለፈጠራ ባለሙያዎች ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ፈጠራ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ መክብብ ታደሰ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ ማህበሩ ለአባላቱ ጥሪ ማቅረቡንና አባላቱም የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን በመስራት ማህበረሰቡን ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በውድድር ተለይተው ለተሻሉት ዕውቅና መሰጠቱ ባለሙያዎች ይበልጥ እንዲሰሩ መነሳሳትን እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።

ኢኖቬሽን የጀርባ አጥንት መሆኑን ገልጸው፣ እንደ ኮቪድ-19 ሁሉ አገራዊ ችግሮች ሲያጋጥሙ ለችግሮች መፍትሔ ለማበጀት ማህበሩና ፈጠራ ባለሙያዎች እንደሚተጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም