ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን እስካከበረች ድረስ ግድቡን ውሃ ከመሙላት የሚያግዳት ኃይል አይኖርም... ምሁራን

67

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግ አስካከበረች ድረስ የግድቡን ውሃ ከመሙላት የሚያግዳት ኃይል እንደማይኖር ፖለቲከኞችና የሕግ ባለሙያዎች አስታወቁ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኤክስፐርቶች ፓናል ሰብሳቢና የተደራዳሪ ቡድን አባል ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው፣ የሕግ ባለሙያና ፖለቲከኛ አቶ ደረጀ በቀለ ፣ የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ በግድቡ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታን ከጀመረችበት የውሃ ሙሌት ለማድረግ እስከተቃረበችበት ጊዜ ድረስ ከህጋዊነትና ፍትሃዊነት ውጭ ምንም አይነት የህግ ጥሰት አላካሄደችም ሲሉም ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የምትከተለውን አብሮ የመልማት አካሄድ ችላ በማለት የውጭ ጫናዎች ሲደረጉ መታየታቸውንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በመጭው ክረምት ግድቡን ውሃ ለመሙላት መዘጋጀቷን ተከትሎ ግብፅ ጫና ለመፍጠር በመሞከሯ ዓለም አቀፍ ፍትሃዊ የሃብት አጠቃቀም መርህን እንደማይቃረን ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታም ይሁን የውሃ አሞላሉ ዓለም አቀፍ መርሆዎችንና አብሮ መልማትን እስካልተቃረነ ድረስ ኢትዮጵያን የውሃ ሙሌቱን የምታስተጓጉልበት ምክንያት የለም ብለዋል።

 ኢትዮጵያ ሃብቷል የመጠቀም ሙሉ መብት ያላት በመሆኑ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይም የህግ ጥሰት የለባትም ያሉት የሕግ ባለሙያና ፖለቲከኛ አቶ ደረጀ በቀለ፤ ይልቁንም ሀገሪቷ የራሷን ሃብት በትክክለኛው መንገድ ለመጠቀም እያደረገች ያለእንቅስቃሴ ነው ብለዋል። 

የህዳሴ ግድብ ኤክስፐርቶች ፓናል ሰብሳቢና የተደራዳሪ ቡድን አባል ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው በበኩላቸው ኢትዮጵያ በግዛቷ የሚገኙትን የውሃ ሃብቶች በሙሉ የአለም አቀፍ ህግ በሚያዘው መሰረት የመጠቀም መብቷን እየተጠቀመችበት መሆኑን ነው የገለጹት።

"በአለም አቀፍ ህግ የተፈቀደውን በአንድ ሃገር ግዛት ውስጥ ያሉ የውሃ ሃብቶችን የመጠቀም ፍትሃዊ የአለም አቀፍ ህጎችን ፣የኢትዮጵያን የሌሎችም ሃገራት ፖሊሲዎችን የሚደግፍ አካሄድ ነው እየተቃወሙ ያሉት የበታች ሀገሮች። '' ብለዋል ኢንጂነር ጌዲዮን።

የኢትዮጵያ ስታራምደው የነበረውና በቀጣይም የምትከተለው አካሄድ የታችኞቹን ተፋሰስ አገሮች ጥቅም እንደማይነካ አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡ በዜጎቿ  አስተዋፅኦ የሚገነባና ሉአላዊነቷንም ለማስከበር በያዘችው አቋም እንደምትፀናም ተናግረዋል።

የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ አባይ ለኢትዮጵያ የተፈጥሮ ስጦታ በመሆኑ በሀብቷ የመጠቀም መብቷን ግብጽ በተሳሳተ መልኩ ማየቷ ትክክል አለመሆኑን ገልጸው፤የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ  በሀገሩ ሉአላዊነትና አንድነት ጉዳይ ላይ አይደራደርም ብለዋል። 


ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው  "ከዚህ ተቆጥበው ወደ ስምምነት ተደርሶ የአካባቢው ሰላም ተጠብቆ የኢትዮጵያና የሌሎችም የናይል ተፋሰስ አገሮች ጥቅም በተጠበቀ መልኩ ይካሄድ የሚል አካሄድ ነው የኛ ይህ አቋም። ትክክልም ነው፣ፍትሃዊም ነው።ለዚህ ነው ምንም አይነት ተፅዕኖ ከየትኛውም አካባቢ ቢመጣ በየትኛውም ድርድር የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ አይሆንም ማለት ነው" በማለት ይገልጻሉ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በሐምሌ ወር የሚጀመር ሲሆን የግድቡ ግንባታም 73 ከመቶ ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም