የምስራቅና አፍሪካ ቀንድ ሀገራት በ3 የተፈጥሮ አደጋዎች እንደሚጠቁ ተነገረ

50

 ግንቦት 14/2012(ኢዜአ) የምስራቅና አፍሪካ ቀንድ ሀገራት በኮቪድ 19፣ በአንበጣ መንጋና በጎርፍ ክፉኛ እንደሚጠቁ ፎክስኒውስ ዘግባል።

ፎክሰ ኒውስ ዛሬ የዓለም አቀፉን የቀይ መስቀል ፌዴሬሽን የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በጎርፍ አደጋ ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ሱማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳና ኡጋንዳ እንደሚጠቁ ጠቁሟል።

 በተጠቀሱት ሀገራት በአደጋው ከ500 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች እንደተፈናቀሉና 300 የሚጠጉ ሰዎችም ለሕልፈት እንደተዳረጉ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ፌዴሬሽን አሳውቋል።

የጎርፍ አደጋው ለኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩም በላይ ለአንበጣ መንጋ መከሰትና መራባት ምክንያት እንደሚሆን ተቋሙ አሳውቋል።

እነዚህም ተደራራቢ ችግሮች ወረርሸኖቹን ለመመከት የሚደረገውን ጥረት አዳጋች እንዳረገውና በርካታ ሰዎችም ለረሃብ እንዳጋለጠ የተቋሙ የአፍሪካ ሪጅን ዳይሬክተር ዶክተር ሲሞን ሚሲሪ ተናግረዋል

በአካባቢው የሚከሰተው መጥፎ የአየር ሁኔታም የምግብ እጥረት እንዲከሰት እንዳደረገና ችግሩን ማባባሱን የገለጹት ኃላፊው፤ ባለፉት አስር ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ የአንበጣ መንጋ ወረርሺኝ እንደሚያስከትልም ኃላፊው ተናግረዋል።

በቀጠናው ከ20 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደተጋለጡ የዓለም አቀፉ የምግብና እርሻ ድርጅት ሪፖርት ማመልከቱን ዘገባው አስታውሷል።

የዓለም ባንክ ለነዚህ ሀገራት የአንበጣ መንጋ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ 500 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ፕሮግራም መንደፉን ዘገባው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም