በቴሌኮም ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ከዛሬ ጀምሮ ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ ተጠየቀ

133

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን በቴሌኮም ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ከዛሬ ጀምሮ ፍላጎታቸውን የሚያሳውቁበት ሰነድ ይፋ ማድረጉን አስታወቀ።

መንግስት የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ከመከላከል ጎን ለጎን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን አጠናክሮ መቀጠሉን ገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ ሁለት የቴሌኮም ፈቃዶችን ለመስጠት የተለያዩ ዝግጅቶችን አጠናቋል።

ከዝግጅቶቹ ውስጥም ''የአለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን አማካሪ መቅጠርና አስተማማኝ የሕግና የቁጥጥር መመሪያ ማውጣት ነው'' ብለዋል። 

እንደ ኢንጂነር ባልቻ ገለጻ ፤ ዘርፉን ለመምራትና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ከ12 ያላነሱ መመሪያዎች ተረቀው የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ውይይት እያደረጉባቸው ነው።

የፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ፣ የተጠቃሚዎች መብት ጥበቃ እንዲሁም የአገልግሎት ጥራት መመሪያዎች ከእነዚህ ውስጥ ይጠቀሳሉ።

በአሁኑ ጊዜም በቴሌኮም ዘርፉ ተጨማሪ ሁለት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ለማስገባት የሚያስችሉ ዝግጅቶች በመጠናቀቃቸው የፍላጎት መጠየቂያ ሰነድ ይፋ ተደርጓል።

''በዚህ መሰረት ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ከዛሬ ጀምሮ ፍላጎታቸውን ማሳወቅ ይችላሉ'' ብለዋል።

ድርጅቶቹ ፍላጎታቸውን ካሳወቁ በኋላም በግልጽ መስፈርቶች በጨረታ የሚወዳደሩበት ሁኔታ መመቻቸቱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ተጨማሪ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ወደ አገር መግባታቸው ለስራ ዕድል ፈጠራ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ኢንጂነር ባልቻ ገልጸዋል።

''በዚህም ለወጣቶች የተለያዩ የስራ ፈቃዶች በመስጠት የስራ ዕድል እንዲያገኙ ይደረጋል'' ብለዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው መንግስት በቴሌኮም ዘርፉ ተጨማሪ ሁለት ኩባንያዎችን ወደ ገበያው ለማስገባት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።

ዘርፉን በተደራጀ መልኩ ለመምራት የኮሙኒኬሽን አዋጅ በማውጣት የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን መቋቋሙን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ጊዜ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ወረርሽኙን ከመከላከል ጎን ለጎን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።

በቴሌኮም ዘርፉ የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ተቋማት ከመንግስት ጋር እስካሁን ምንም አይነት ንግግር እንደሌላቸው የገለጹት ዶክተር ኢዮብ፤ ''ስራው በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚከወን ነው'' ብለዋል።

እንደ ዶክተር እዮብ ገለጻ፤ መንግስት የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሚያከናውናቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል።

ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ የሚደረጉ ሁለት ኩባንያዎችም መንግስት የቴሌኮም ዘርፉን ለመምራት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እንደሚሰሩም አስገንዝበዋል።


የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ነሐሴ 6 ቀን 2011 ዓ.ም በኮሙኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 1148/2011  የተቋቋመ ነው።

ተወዳዳሪ የገበያ ሥርዓትን በማበረታታት የተጠቃሚዎችን ተደራሽነትና ፍላጎት ያሟላ፣ ጥራቱን የጠበቀ፣ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ያገናዘበ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመላ አገሪቱ ማስፋፋት ዋነኛ ዓላማው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም