ህዝቡን ከኮሮና ቫይረስ መጠበቅ ከሁሉም ነገር ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ ነው….የብልጽግና ፓርቲ

86

ሐረር (ኢዜአ)ግንቦት 13/2012.በአሁኑ ወቅት ህዝቡን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከሉ ተግባር ከሁሉም ነገር ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት በመላ ሃገሪቱ እየተሰራ መሆኑን የብልጽግና የፓርቲ አስታወቀ።

የፓርቲው የፖለቲካና ሲቪክ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ ትላንት በሀረር ከተማ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር በአፍጥር ፕሮግራም በተካፈሉበት ወቅት እንደገለጹት ወቅቱ ከማንኛውም አጀንዳ በተለየ መልኩ ቅድሚያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መከላከልን የሚጠይቅ ነው።

"እንደ ብልጽግና ፓርቲ የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል አንጻር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ቀኝት እያደረግን ነው" ያሉት ኃላፊው በተለይም በህብረተሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ቤት ለቤት በመሄድ ጭምር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

"አቅመ ደካሞችን ከመደገፍ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባስተላለፉት 'ማእድ የማጋራት' መልእክት ያለው ለሌለው በማካፈል በተለይ የረመዳንን ጾም ማጠናቀቅና በቀጣይም ይህን ተግባር ሁሉም ሊያጠናክረው ይገባል" ብለዋል።

የምስራቁ የሃገራችን ማህበረሰብ ያለው ማህበራዊ ቁርኝት ጠንካራ መሆኑን ገልጸው "ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ ለጊዜው ይህንን መግታት ይገባል" ሲሉ አስገንዝበዋል።

"የብለፅግና ፓርቲም በየክልሉ ቫይረሱን ከመከላከል እና ከመቆጣጠር አንፃር በትኩረት እየተንቀሳቀሰ ነው" ያሉት ዶክተር አለሙ ህብረተሰቡም በመከላከል ስራው ላይ የተጠናከረ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

እንዲሁም አርሶና አርብቶ አደሩ፣ነጋዴውና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች የእለት ተግባራቸውን ሲያከናውኑ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከወረርሽኙ በመጠበቅ በኢኮኖሚው ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይከሰት እንዲረባረቡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም