ህወሓት በክልል ደረጃ አካሂዳለው የሚለው ምርጫ ሕገ ወጥ በመሆኑ ከድርጊቱ ሊቆጠብ ይገባል ... የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ

65

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ በክልል ደረጃ ምርጫ አካሂዳለው ማለቱ ሕገ ወጥና የአገሪቷን ሕጎች የሚንድ በመሆኑ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ አሳሰበ።

የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ምርጫ ማራዘምን ጨምሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የአመራር አባላቱ ቀደም ሲል በ'ህወሓት' ውስጥ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውንና አሁን ከአገራዊ ለውጡ ጋር መሰለፋቸውን ባወጡት ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አሳውቀዋል።

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ዋና አጀንዳ በስሙ ሲነገድበት የቆየውን የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግና ቀጣይ ዕጣ ፈንታውን ብሩህ ማድረግ እንደሆነም ተመልክቷል።

የትግራይ ሕዝብ ለመብቱ ዋጋ የከፈለና ከኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህቶቹ ጋር በሠላም መኖር የሚፈልግ ነው ብለዋል በመግለጫቸው።

የክልሉ ሕዝብ የግል ስልጣናቸውን ማደላደል በሚሹ በጥቂት ቡድኖች ታጥሮ የተገለለና ዛሬም ታፍኖ ያለ መሆኑንም መግለጫው ያትታል።

ሕዝቡ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ውስጥ ባለበት ወቅት 'ምርጫ ካልተደረገ' የሚል ግትር አቋም ማራመድ ለህዝብ ደህንነት ደንታ ቢስነትን ማሳየት ነውም ብሏል።

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ አመራር አባላት በመንግስት በኩል ምርጫውን ለማራዘም እየተከናወኑ ያሉ ሕግ መንግስታዊ ሂደቶችንም ደግፈዋል።

"በክልል ደረጃ ምርጫ ማካሄድ የማይቻልና ኢ-ሕገ መንግስታዊ ነው" ያለው መግለጫው ህወሓት በክልል ደረጃ ምርጫ አካሂዳለው ብሎ መነሳቱ ህገ ወጥ በመሆኑ ሊቆም ይገባል ብሏል።

የትግራይ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት ብዙ ዋጋ የከፈለና ፍላጎቱም ሠላም፣ ልማትና ፍትህ መሆኑ ሊታወቅ ይገባልም ብሏል መግለጫው።

ከወረርሽኙ ባለፈ በክልሉ አፈና እየተካሄደ በመሆኑ ምርጫ ማካሄድ ከባድ ነው የሚሉት የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሁል ናቸው።

በክልሉ ህወሓት በሚመራው መንግስት የመናገር ነጻነትና የፖለቲካ ሃሳብ ማንሸራሸር ተገድቧል ነው ያሉት።

ከዚህም አልፎ በክልሉ ወጣቶች የሚገደሉበት አሳሳቢ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ይህ ሁኔታ ለትግራይ ህዝብ የማይገባ በመሆኑ እየታገለ ይገኛልም ብለዋል። 

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ የለውጥ ስራዎች ድጋፍና ክትትል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኃፍታይ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው ፓርቲው የትግራይ ተወላጆችን በስፋት ለማሳተፍ ይንቀሳቀሳል ይላሉ።

በመዲናዋ የሚገኙ አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች ከብልጽግና ፓርቲ ጋር እንደሚንቀሳቀሱ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የፓርቲው አመራር አባላትም በክልሉ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ህወሓት ጠቃሚ ያልሆነ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ ወቅት ምርጫ ለማካሄድ ማሰብን ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የራስን ፍላጎት ለማስቀደም የሚደረግ ጥረት ነው ብለውታል።

በማንኛውም ሁኔታ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የህዝብ ፍላጎትና ጥቅም መሆኑንና የግል ፍላጎት ቀጥሎ የሚመጣ ጉዳይ እንደሆነ ህወሓት ሊረዳ ይገባል ብለዋል።

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር ሙሉ ነጋም ፓርቲው እንደሚባለው አሃዳዊ ሳይሆን አቃፊ ነው ይላሉ።

ለውጡ አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር፣ ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ስርዓቱን ማጠናከርን ዓላማ አድርጎ የሚጓዝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ብልጽግና በረጅም ጊዜ ሂደት ጠንካራ አገረ መንግስትና ብሔረ መንግስት የመገንባት ዓላማ ያለው ፓርቲ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም