የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን የመከላከል ጥንቃቄን ማድረግን ጨምሮ ምርጫ ለማካሄድ ተጨማሪ 13 ወራት ሊወስድ ይችላል - ቦርዱ

68

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን የመከላከል ጥንቃቄ ማድረግን ጨምሮ ምርጫ ለማካሄድ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀትና 13 ወራት የሚወስድ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ተናገሩ።

የህገ-መንግስት ትርጉም ጥያቄ ላይ ያተኮረ የባለሙያዎች ማብራሪያ በተካሄደበት ወቅት ምክትል ሰብሳቢው ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት የኮሮና ድቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ተጽዕኖ ምርጫውን በተያዘለት ጊዜ ማድረግ እንዳልተቻለ አብራርተዋል።

ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማካሄድ ባለመቻሉ ቦርዱ ለሌላ ተጨማሪ ወጪ መዳረጉን አቶ ውብሸት ባቀረቡት የዳሰሳ ጥናት አመላክተዋል።

በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ምዝገባ በ30 ቀናት፣ የእጩዎቸ ምዝገባን በ15 ቀናት እና የምረጡኝ ቅስቀሳ በ90 ቀናት እና ለመራጮች የሚሰጥ ትምህርት በ121 ቀናት ውስጥ ለማካሄድ ታቅዶ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአንድ የምርጫ ጣቢያም እስከ 1 ሺህ 500 ሰው   የሚሳተፍባቸው 50 ሺህ ምርጫ ጣቢያዎች  የማዘጋጀት ፣ 250 ሺህ ምርጫ አስፈጻሚዎችን በመመልመል ለማሰልጠን ዝግጅት  ሲደረግ እንደነበርም  አስታውሰዋል።

በአማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎች የመራጮች ምዝገባ ሰነዶች ማሳተም፣ የምርጫ ቁሳቁሶችን በአስተማማኝ ቦታ ለማስቀመጥ እቅድ ተይዞ ነበር ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወረርሽኙ በመከሰቱ ቦርዱ የዳሰሳ ጥናት አድርጎ በጥናቱ የመጀመሪያ ግኝት ላይ መጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማድረጉን አስታውሰዋል።

ቦርዱ የኮሮና ቫይረስን ተጽዕኖ በተመለከተ በዓለም አቀፍ፣ በአገር አቀፍ አዝማሚያ እና ጤና ባለሙያዎች ግብዓትን በመጠቀም ወረርሽኙ በምርጫው ላይ የሚያሳድረውን ጫና መገምገሙን ገልጸዋል።

በዚህም ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተጣሉት ክልከላዎች ሁለት ሳምንት ብቻ የሚቆዩ ቢሆን ወደ ተቋረጡት ስራዎች ተመልሶ ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ማከናወን እንደሚቻል፤ ክልከላው ከሁለት ሳምንት በላይ ከዘለቀ ምርጫውን ለማካሄድ እንደማይቻል ዳሰሳው ማሳየቱን ገልጸዋል።

ምርጫ እንደማይካሄድ ከተረጋገጠ በኋላ ቦርዱ በቀጣይ ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።

''ምርጫው ከተሰረዘ በኋላ የመራጮች ምዝገባን በኦንላይን መመዝገብ እና የዳታ ቤዝ ግንባታ፣ የእጩዎች ምዝገባን ወደ ዲጂታል መለወጥ፣ እጩ ወኪሎች፣ ሲቪል ማህበራትና እውቅና የተሰጣቸው ጋዜጠኞችን በዲጂታል የመመዝገብ ስራ ተሰርቷል'' ብለዋል።

የመራጮች ምዝገባ፣ የእጩዎች ምዝገባ፣ ድምጽ አሰጣጥ በአነስተኛ ቴክኖሎጂ እገዛ የሚካሄድ በመሆኑ፣ ካሉት የመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ የደህንነት እና የልማት ሁኔታ በኦንላይን ምርጫ ለማድረግ አመቺ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

ቦርዱ የወደፊት አቅጣጫን በተመለከት በሶስት ክፍሎች ግምገማ ማካሄዱን አቶ ውብሸት አብራርተዋል።

የመጀመሪያው ክፍል ስጋቶችን ለመቀነስ የሚረዱ ርምጃዎችን ያየ ሲሆን በሁለተኛ ክፍል ደግሞ ስጋቶቹ በስራ ዘመቻና በበጀት ላይ ያላቸውን እንድምታ ለማወቅ መሆኑን ገልጸዋል።

''በሶስተኛ ክፍል በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማካሄድ ይሆናል'' ብለዋል።

ቦርዱ በወረርሽኙ ምክንያት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ምን ሊሆኑ ይችላል በሚል ባደረገው ዳሰሳ የኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ስርጭት ቢኖር የጊዜ ሰሌዳ ሊጨምር እንደሚችል፣ የምርጫ ቁሳቁሶች ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል፣ ከመንግስት በጀት የሚገኝ ድጋፍ አነስተኛ ሊሆን እንደሚችልና የዓለም አቀፍ ድጋፍ ሊቀንስ እንደሚችል አስቀምጧል።

በዚህ መሰረት ቦርዱ ሁለት የጊዜ ሰሌዳዎችን ማስቀመጡን የገለጹት ምክትል ሰብሳቢው፤ የመጀመሪያው አማራጭ ቦርዱ ተጨማሪ ግምቶችን ሳይወስድ የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ በምርጫ አካሄድ ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል አመልክተው፤ ''በዚህ አማራጭ አጠቃላይ ምርጫውን ለማስፈጸም ተጨማሪ ከ139 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል'' ብለዋል።

''በሁለተኛ አማራጭ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ የሚቀጥል ከሆነ ምርጫ ቦርድ በተወሰኑ ገደቦች ምርጫ ሊያካሂድ ይችላል'' ብለዋል።

ጤናን የተመለከቱ መመሪያዎችን ለማጽደቅ ተጨማሪ 90 ቀናት እንደሚያስፈልጉ፣ ለመራጮች ምዝገባ በተራዘመ ጊዜ የሚካሄድ እና በአንድ ምርጫ ጣቢያ የመራጮች ቁጥር በአንድ ሺህ የሚገደብ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር በ10 ሺህና የአስፈጻሚዎችም ቁጥር በ30 ሺህ እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

የአስፈጻሚዎች ስልጠና፣ የመራጮችና የእጩዎች ምዝገባ ቀን መጨመርና የምረጡኝ ዘመቻ ቀን መጨመር በበጀት ላይ ጫና እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

በአጠቃላይ የኮሮና ቫይረስን ጥንቃቄ በማካተት ምርጫ ማካሄድ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት እንደሚያስፈልግና 13 ወራትን የሚፈጅ ሂደት መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም