በማዳበሪያና ምርጥ ዘር እጥረት ምክንያት የመኸር ሥራችንን ማከናወን አልቻልንም....አርሶ አደሮች

66
ደብረ ብርሃን ሰኔ 28/2010 በማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረትና መዘግየት ምክንያት የመኸር እርሻ ሥራቸውን በተገቢው መንገድ ማከናወን እንዳልቻሉ በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን የቀዎት ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ። የቀወት ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ተፈራ ደስታ  እንደገለጹት በማዳበሪያና ምርጥ ዘር እጥረት ምክንያት መሬታቸውን ያለ ግብዓት ለመዝራት ተገደዋል፡፡ በመኸሩ 16 ኩንታል ማዳበሪያና አንድ ኩንታል ተኩል የቢራ ገብስ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላና ጤፍ ምርጥ ዘሮች ለመጠቀም አቅደው እስካሁን ዘጠኝ ኩንታል ማዳበሪያና ግማሽ ኩንታል ምርጥ ዘር ብቻ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ በእዚህም "ቀድመው የሚዘሩ የማሽላና የበቆሎ ሰብሎችን ያለማዳበሪያ ለመዝራት ተገድጂያለሁ" ብለዋል። ሌላው አርሶ አደር ወርቁ ሞላ 11 ኩንታል ማዳበሪያና አንድ ኩንታል የጤፍ፣ የስንዴ፣ የበቆሎ፣ የማሽላና የምስር ምርጥ ዘር ለመጠቀም ቢያቅዱም በአቅርቦት እጥረት ያቀዱት አለመሳካቱን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን 6 ኩንታል ማዳበሪያ ብቻ ማግኘታቸውንና ምንም አይነት ምርጥ ዘር አለማግኘታቸውን ለሚመለከተው አካል ቢያሳውቁም መፍትሄ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል። በእዚህም የማመርተው ምርት ይቀንሳል የሚል ስጋት እንደገባቸው ገልጸዋል፡፡ የግሸ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የግብዓት አቅርቦትና የገጠር ፋይናንስ ቡድን መሪ አቶ አበበ ጎላ በበኩላቸው በማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት አርሶ አደሩ በጠየቀው ልክ ለማስተናገድ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮች 4 ሺህ 495 ኩንታል ማዳበሪያ እንዲቀርብላቸው ቢጠይቁም እስካሁን የቀረበው 2 ሺህ 576 ኩንታል ብቻ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ አርሶ አደሩ የሚፈለገውን ግብዓት ባለማግኘቱ ማሽላና በቆሎ ያለማዳበሪያ እየዘራ መሆኑ በምርት ዘመኑ የታቀደውን ምርት ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡ በሰሜን ሽዋ ዞን ግብርና መምሪያ የግብዓት አቅርቦትና ስርጪት ቡድን መሪ ወይዘሮ ሙሉ ዘገዬ በበኩላቸው ችግሩ አገር አቀፍ መሆኑንና በእጃቸው ያለውን ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በአግባቡ ለማዳረስ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ "ለተያዘው የመኸር ወቅት 653 ሺህ 500 ኩንታል ማዳበሪያ ለማሰራጨት ቢታቀድም በአቅርቦት መዘግየት ምክንያት እስካሁንም የተሰራጨው ከ260 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ብቻ ነው" ብለዋል። ችግሩን ለመከላከል ያለውን ማደበሪያ አመጣጥነን ለማሰራጨት ብንሞክርም የዘገዩት በጣም ተጎጂ በመሆናቸው በቀሪው ጊዜ እጥረት ወዳለበት ቦታ ለማዳረስ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡ በወደብ አካባቢ በተፈጠረ የትራንስፖርት መጓተት ምክንያት ፈጥኖ ያልደረሰው ቀሪው ማዳበሪያ በቅርቡ ይደርሳል በሚል በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንና እንደደረሰም ፈጥኖ እንደሚሰራጭ አመልክተዋል። ዞኑ ካቀደው 18 ሺህ 533 ኩንታል ምርጥ ዘርም 8 ሺህ 117 ብቻ ወደአካባቢው መደረሱ ያመለከቱት ቡድን መሪዋ፣ ከክልሉ በጨረታ የተገኙ ምርጥ ዘሮች ጥራታቸው የተጓደለ በመሆኑ አርሶ አደሩ ተጨማሪ እንዳይጠብቅ አመልክተዋል። በቀጣይ የሚሰራጭ ምርጥ ዘር ባለመኖሩ አርሶ አደሩ በፊት የተጠቀመውንና አሁን የደረሰውን ምርጥ ዘር በአግባቡ ሊጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በዞኑ በተያዘው የመኸር ወቅት ከ509 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም