የአውሮፓ ሀገራት ለኮቪድ 19 ግርሻ ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው ተባለ

94

 አዲስ አበባ  ግንቦት 13/2012 (ኢዜአ)የአውሮፓ ሀገራት ለኮቪድ 19 ወረርሺኝ መከላከያ ክትባትም ሆነ መድኃኒት እስካልተገኘ ድረስ ለሁለተኛው ዙር የቫይረሱ ጥቃት ራሳቸውን ማዘጋጅ እንደለባቸው የህብረቱ የበሽታዎች ቁጥጥር ኃላፊ ዶከተር አንደሪያ አሞን አሳሰቡ።


እስከ አሁን ጥቂት ሰዎች ብቻ ቫይረሱን የመከላከል አቅም ያጎለበቱት የሚሉት ኃላፊዋ፤ እስከ አሁን ቫይረሱን ማሸነፍ አልቻልንም ማለታቸውን ዴሊ ሜል ዘግቧል።


ከ15 ከመቶ በታች የህብረቱ አባል ሀገራት በቫይረሱ መጠቃታቸውን የሚናገሩት ዶክተር አንድሪያ፤ አብዛኛው ሕዝብ የቫይረሱ ተጋላጭ የሚሆነው ወደፊት ነው ብለዋል።


በሳይንሳዊ ስሙ ሳርስ ኮቪድ 2 (SARS-COV-2) እየተባለ የሚጠራው ቫይረሱ መቼና በምን ሁኔታ ከኅብረተሰቡ ሊጠፋ እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአውሮፓ በቫይረሱ አዲስ የሚያዙ ና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣት የቫይረሱን ጦርነት እንዳሸነፍን አድርገን መቆጠር እንደሌለበት የዘርፉ ኤክስፐርቶች ማስጠንቀቃቸውን ዴሊሜል በዘገባው አመልክታል።


ሁሉም ሳይንቲስቶች በሚባል ደረጃ የቫይረሱ ክትባት ወይም መድኃኒት ካልተገኘ ቫይረሱ ዳግም መቀስቀሱ እንደማይቀር እንደሚስማሙ ዘገባው አመልክቷል።
የቫይረሱ ግርሻ በፈረንጆቹ ክረምት ላይ ይቀሰቀሳል ተብሎ እንደተሰጋም ዘገባው አስታውቋል።
በአውሮፓ እስከ አሁን 1ሚሊዮን 740 ሺሕ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ 164 ሺሕ 349 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም