በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች ከ927 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለዘር ተዘጋጅቷል

61

ደብረ ማርቆስና ወልድያ፤ ግንቦት 13/2012(ኢዜአ). በምስራቅ ጎጃምና በሰሜን ወሎ ዞኖች ለመጪው የመኸር ወቅት በዘር የሚሸፈን 927 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶና ለስልሶ ዝግጁ መሆኑን የየዞኑ ግብርና መምሪያዎች ገለፁ ።

በምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አበባው እንየው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በዘንድሮው የመኸር አዝመራ የምርት መቀነስ እንዳያጋጥም ከወዲሁ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።

በዞኑ በዘር ለመሸፈን ከታቀደው 689 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን እስከ 4ኛ ዙር ድረስ ተደጋግሞ እንዲታረስ ተደርጓል ብለዋል።

የክረምቱ ዝናብ መጣል መጀመሩን ተከትሎ ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን እራሳቸውን ለኮሮና ቫይረስ በማያጋልጥ መልኩ የዘር ስራቸውን እንዲያከናውኑ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም ከ10ሺህ 500 ሄክታር በላይ ማሳ በበቆሎ፣ በገብስ እና በማሽላ ዘር የተሸፈነ መሆኑን ጠቁመው፤ በእርሻ ሥራው ላይ ዘጠኝ ትራክተሮች ገብተው እገዛ ማድረጋቸው ታውቋል።

የምርት ማሳደጊያ ግብዓትን በመጠቀም፣ በኩታ ገጠምና በመስመር በመዝራት በመጪው የመኸር አዝመራ 21 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።

የአነደድ ወረዳ የጉዳለማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይግዛው ደጉ በሰጡት አስተያየት "ቀደም ብየ ማሳየን ደጋግሜ በማረስ ማዘጋጀት በመቻሌ ዝናቡ እንደ ጣለ ግማሽ ሄክታር መሬቴን  በበቆሎ መሸፈን ችያለሁ" ብለዋል።

በተያያዘ ዜና በሰሜን ወሎ ዞን በመጪው መኸር ከ238 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለመሸፈን እየተሠራ መሆኑን በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አባይ መልኩ ገልጸዋል።

የምርት እድገትን ለማስጠበቅም እስካሁን 86 ሺህ 620 ኩንታል ዘመናዊ ማዳበሪያ እየተሰራጨ መሆኑን ጠቁመው ሶስት ሚሊዮን ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ቀድሞ በማሳ እንዲበተን ተደርጓል።

484 ሺህ 261 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱም ታውቋል ።

በጉባላፍቶ ወረዳ የቀበሌ 04 ነዋሪ አርሶ አደር መኮንን አሊ እንደገለፁት ዝናቡ ቀድሞ በመጀመሩ ማሽላና በቆሎ መዝራታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም