በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የአንበጣ መንጋን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው

60

ባህር ዳር/ ነቀምቴ /ግንቦት 13/2012(ኢዜአ) በምስራቅ አማራ አካባቢ እና በአሮሚያ ምስራቅ ወለጋ ዞን የአንበጣ መንጋን ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

የአንበጣ መንጋ ዘንድሮ  በምስራቅ አማራ መከሰቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ አስረድተዋል።

በኦሮሞ ብሄረስብ  አስተዳደር፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች የስጋት ቀጠናዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ከየዞኖቹ የተውጣጣ  ግብረ ኃይል በማቋቋም ጠንካራ የክትትልና አሰሳ ሰራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ግብረ ኃይሉ በተጨማሪ የአንበጣ መንጋው ክስተት በሚታይበት አካባቢ የኬሚካል ርጭትና ሌሎች የመከላከል ስራዎች ለማከናወን ዝግጅት  እያደረገ  ነው።

በተጨማሪም በፌዴራል መንግስት አስተባባሪነት በአፋር ክልል በረሃማ አካባቢዎች በኩል ሊከሰት ይችላል ተብሎ የሚታሰብን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በጥምረት እየተሰራ መሆኑን  ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅም የአንበጣ መንጋው በተከሰተ ወቅት በአካባቢው ለሚገኝ የግብርና ባለሙያዎች መጠቆም እንዳለበት አሳስበዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን  ቃሎ ወረዳ የቀበሌ 020  አርሶ አደር አህመድ ጉግሳ በሰጡት አስተያየት የአንበጣ መንጋ ባለፈው  ዓመት ያደረሰባቸውን የምርት ኪሳራ ለማካካስ አንድ ሄክታር መሬታቸውን ደጋግመው በማረስ  በበቆሎ ዘር ለመሸፈን  የቅድመ ዝግጅት ስራ  ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም የአንበጣ መንጋው አሁንም በመስኖ በለማ ሰብል ላይ በመከሰቱ በቀጣዩ የመኸር ወቅት የአምናውን  ዓይነት ጉዳት ሊያደርስ ይችላል በሚል መስጋታቸውን  ገልፀዋል።

ባህላዊ የመከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም ለመከላከል ቢሰሩም ማስወገድ ባለመቻሉ የመንግስት ድጋፍ እንደሚያሻቸውም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ምስራቅ ወለጋ ዞን  አምስት ወረዳዎች  የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የአዝርዕት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፋንታ አሰበ እንደተናገሩት፤ የአንባጣ መንጋው የተከሰተው በዋማ አገሎ፣ ቦነያ ቦሼ፣ ጎቡ ሰዮ፣ ዲጋና ጉደያ ቢላ ወረዳዎች ውስጥ ነው፡፡

እስካሁን  ጉዳት እንዳላደረሰ ጠቁመው፤ ሕዝቡ  ባህላዊ ዘዴን  በመጠቀም ለመከላከል ጥረት እያደረገ መሆኑን  አመልክተዋል ፡፡

የዋማ አገሎ ወረዳ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ለማ በበኩላቸው  የአንበጣ መንጋው ግንቦት 9 እና 10 ቀን 2012ዓ.ም በአምስት ቀበሌዎች መታየቱን ተናግረዋል።

የመንግሥት ሠራተኞች፣ አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎች በጋራ በመውጣት ከአካባቢያቸው ማባረራቸውን አመልክተዋል።

በስምንት ቀበሌዎች የታየው መንጋው  በህብረተሰቡ ተሳትፎ በባህላዊ ዘዴ መከላከል መቻሉን የተናገሩት ደግሞ የቦነያ ቦሼ ወረዳ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ ደረጀ ታደሰ ናቸው።

የአንበጣ መንጋ በሁለቱም ወረዳዎች  ዳግም ተመልሶ ሊመጣ ይችላል በሚል ስጋት አርሶ አደሩና  የግብርና ባለሙያዎች በጥንቃቄ እየተከታተሉ ለመከላከል ዝግጁ  መሆናቸውን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም