በህገወጥ መንገድ 800 ኩንታል ሲሚንቶ ሲያጓጉዙ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች ተያዙ

56

ባህርዳር ፣ ግንቦት 13/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) በባህርዳር ከተማ አስተዳደር በህገወጥ መንገድ ለገበያ የቀረበ 800 ኩንታል ሲሚንቶ ሲያጓጉዙ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የከተማው ግብረኃይል ገለፀ ።

የግብረኃይሉ አባልና የከተማው ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙላለም ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በህገ ወጥ መንገድ 800 ኩንታል ሲሚንቶ ለመሸጥ ሲሞክሩ ነው ።

ህጋዊ የንግድ ፈቃድ የሌላቸው ግለሰቦች የሲሚንቶ ምርቱን በሁለት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ባህርዳር ከተማ በማስገባት አየር በአየር ለመሸጥ ሲሞክሩ በህብረተሰቡ ጥቆማ በከተማው ገበያ ማረጋጋት ግብረ ኃይል አማካኝነት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ።

ምርቱ ምንም አይነት የንግድ ፈቃድ በሌላቸው ግለሰቦች ከደርባንና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በህገ ወጥ መንገድ የመጣ መሆኑንም አቶ ሙላለም አስረድተዋል ።

ግለሰቦቹ በአሁኑ ወቅት በ9ኛ ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው እየተጣራ ነው ብለዋል ።

የሲሚንቶ ንግድ  እንደ ሀገር ችግር ያለበትና በደላላ እየተመራ ያለ በመሆኑ ህገወጥነት እንዲስፋፋና ዋጋው እንዲያሻቅብ አድርጎታል ።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ዳይሬክተር አቶ አማረ ጌታቸው በበኩላቸው እየተስተዋለ ያለውን ህገወጥ ንግድና የዋጋ ንረት ስርዓት ለማስያዝ ቢሮው እየሰራ ይገኛል።

ህገወጥ ንግድንና የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ባለፈው ሳምንት በባህር ዳር የተጀመረው የክትትልና ቁጥጥር ስራ በሁሉም ዞኖች ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ስምሪት ተሰጥቶ ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል።

ህብረተሰቡም ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል የጀመረውን ጥቆማ ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ግንዛቤውን የማሳደግ ስራ በተዋረድ እየተሰራ እንደሆነም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም