የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች የኮቪድ 19 እንዳበቃ የገጽ ለገጽ ትምህርት ይቀጥላሉ

52

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዳበቃ የገጽ ለገጽ ትምህርታቸውን እንደሚቀጥሉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ገለጹ።

የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ኦንላይን ተፈትነው ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁበት ሁኔታ መኖሩንም አመልክተዋል።

ፕሮፌሰር ሂሩት ለኢዜአ እንደተናገሩት ዓለም አቀፉ የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ የዓለም የአኗኗርና የሥራ ሁኔታ ቀይሯል።

ወረርሽኙን ተከትሎ የመማር ማስተማር ሂደቱ ከገጽ ለገጽ ወደ ኦንላይን በመቀየር በከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች መቀየሩን ተናግረዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ሂሩት ገለጻ የመማር ማስተማሩን ሂደት በቴክኖሎጂ እገዛ ለመስጠት ችግሮች ያጋጥማሉ።

ከነዚህም የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትና የመማሪያ ቁሳቁስ አቅርቦት እጥረት ይጠቀሳሉ።

የኢንተርኔት መቆራረጥና ተደራሽነት ዓለም አቀፍ ችግር መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ተማሪዎች ባገኙት አጋጣሚና ግብዓት በመጠቀም ከትምህርት መለየት የለባቸውም ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፣ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ተመሳሳይ የትምህርት ዕድል ባላገኙበት ሁኔታ በኦንላይን ብቻ ተሰጥቷል ተብሎ ወደ ቀጣዩ የትምህርት ደረጃ ማሸጋገር ተገቢ አይደለም።

በመሆኑም በተለይ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች የወረርሽኙ መገታትን ተከትሎ የገጽ ለገጽ ትምህርታቸውን  እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ የሁለተኛና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ኢንተርኔትና የማስተማሪያ ግብዓት የሚያገኙበት ዕድል ስላለ ኦንላይን ተፈትነው ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ አዳጋች አይሆንባቸውም።

በአገር አቀፍ ደረጃ የመማር ማስተማሩን ሂደት ከገጽ ለገጽ ወደ ኦንላይን የመቀየር ዕቅድ መኖሩን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ሂሩት፣ ይሁንና የኮሮና ወረርሽኝ የትምህርት መሠረተ ልማቱ ሳይሟላ መከሰቱ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።

''በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው ላይ እንደተቀመጠው በቀጣይም በቴክኖሎጂ በመታገዝ የትምህርት ተደራሽነትን እናሰፋለን'' ነው ያሉት።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የከፍተኛ ተምህርት ተቋማት ተማሪዎች በቤታቸው በተለያዩ የመማሪያ ዘዴዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም