ከባንክ በሚወጣ ጥሬ ገንዘብ ላይ የተጣለው ገደብ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ይከላከላል

181

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ግለሰቦችና ተቋማት ከባንክ በሚያወጡት ጥሬ ገንዘብ ላይ የተጣለው ገደብ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚያሳድግ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ገለጸ።

ልዩ ሁኔታ ሲያጋጥም ተጨማሪ ገንዘብ ማውጣት ይቻላልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ተጠንቶ የቀረበለትን በቀን የሚወጣውን የጥሬ ገንዘብ ገደብ ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል።

በዚህም ተቋማት በቀን 300 ሺህ ብር በወር 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፣ ግለሰቦች ደግሞ በቀን 200 ሺህ ብር በወር አንድ ሚሊዮን ብር ብቻ ማውጣት ይችላሉ።

ማኅበሩ አሰራሩ ለአገሪቱ ኢኮኖሚና ለባንኮች ዘመናዊነት የሚኖረውን አስተዋጽኦ በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና የማኅበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አቤ ሳኖ እንደገለጹት የደንበኞች የብር ኖት አያያዝ ለጉዳት የተጋለጠ ነው።

በኢትዮጵያ ከባንክ ውጭ በግለሰቦችና ተቋማት የሚዘዋወረው ገንዘብ ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ደግሞ ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው ገልጸዋል።

በጥሬ ገንዘብ ማውጣት ላይ የተጣለው ገደብም የብር ኖቶች በባንኮች ተቀማጭ ሆነው ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ያግዛል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረገውን የገንዘብ ዝውውር በመግታት የአገሪቱን ኢኮኖሚና የባንኮችን ዘመናዊነት እንደሚያሳድገው አቶ አቤ አስረድተዋል።

ደንበኞች ገንዘባቸውን በሒሳብ ቁጥር፣ በሲፒኦ፣ ያለገደብ እንዲሁም በኢንተርኔትና ሞባይል ባንኪንግ ማዘዋወር ይችላሉ ብለዋል።

"ገንዘብ የግብይት ስርዓትን ከማሳለጥ ውጭ ለሌላ ዓላማ መዋል የለበትም" ያሉት አቶ አቤ፤ በቀን ከ100 ሺህ ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ የሚያወጡ ግለሰቦች እንዳይታወቅባቸው የሚፈልጉት ነገር ሊኖር እንደሚችል ገልጸዋል።

የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የማህበሩ አባል አቶ ፀሐይ ሺፈራው እንደሚናገሩት በእጅ የሚያዘው የገንዘብ መጠን ገደብ ሊኖረው ይገባል።

ነገር ግን ከተጣለው ገደብ በላይ ጥሬ ገንዘብ የሚያስፈልግበት አጋጣሚ ወይም ችግር ሲፈጠር በልዩ ሁኔታ ፈቃድ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የቴሌኮሙኒኬሽን ችግር ሊኖር እንደሚችል የገለጹት አቶ ፀሐይ፤ ነገር ግን ከፍተኛ ወጪ የተደረገባቸው የሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ ቴክኖሎጂዎች በበቂ ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዳልዋሉ ገልጸዋል።

በመሆኑም በግለሰብ ደረጃ መጠነኛ ችግር ይከሰታል ተብሎ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚመጣውን አደጋ በዝምታ ማየት የለብንም ብለዋል።

የዳሽን ባንክ ፕሬዚዳንትና የማኅበሩ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አስፋው ዓለሙ በበኩላቸው ኅብረተሰቡ በከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት የሚታተም ገንዘብ ቤት ውስጥ ማስቀመጥ ወንጀል መሆኑን መረዳት ይገባዋል ይላሉ።

ከባንክ በሚወጣው በጥሬ ገንዘብ ላይ የተጣለውን ገደብም ወደ ዘመናዊ የባንክ ሥርዓት የሚያስገባ ሂደት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም