ማህበሩ በሐዋሳ ከተማ የሳኒታይዘር ማምረቻ ፋብሪካ አስገነባ

82

ሀዋሳ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል የሚረዳ የሳኒታይዘር ማምረቻ ፋብሪካ አስገነባ።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት  አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ ሄሌን ደበበን ጨምሮ የተለያዩ ስራ ኃላፊዎች ማህበሩ ያስገነባውን የሳኒታይዘር ማምረቻ  ጎብኝተዋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተሾመ ታከለ በጉብኝቱ ወቅት  እንደገለጹት ማህበሩ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ አደጋ ሲያጋጥም ቀድሞ ሰብአዊ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ደግሞ የማህበሩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በጎ ፈቃደኞን በማስተባበር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ደግሞ ሳኒታይዘር ለማምረት ፋብሪካ መገንባቱን አስታውቀዋል።

ፋብሪካው በሁለት ቀናት ውስጥ ማምረት ሲጀምር በክልሉ በሚገኙ የማህበሩ 21 መድኃኒት ቤቶችና ሌሎችም ጤና ተቋማት አማካኝነት ለህብረተሰቡ በዝቅተኛ ዋጋ በማቅረብ ተደራሽ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

"የፋብሪካው ስራ መጀመር በተለይ የጤና ተቋማት ምርቱን ለማግኘት የሚያባክኑትን ጊዜ ፣ ከጥራት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ስጋቶችና ቅሬታዎች የሚያስቀር ነው" ብለዋል።

በቀን 3 ሺህ ሊትር ሳኒታይዘር የማምረት አቅም እንዳለውና የተጠቃሚዎች ፍላጎት ታይቶ ከዚህ በእጥፍ ማሳደግ እንደሚቻል አመልክተዋል።

በቀላል ቴክኖሎጂ የተገነባው ፋብሪካ በቅድሚያ ለኮሮና መከላከል ስራ እንዲያገለግል ታስቦ ቢሆንም በዘላቂነት ተላላፊ በሽታዎች እያስከተሉ ያሉ ስጋቶች ለመከላከል ስራም ያግዛል ተብሏል።

ቫይረሱ ከተከሰተ ጀምሮ የንጽህና መጠበቂያ ግብዓት ለማግኘት ህብረተሰቡ እየተቸገረ መሆኑን በመረዳት ፋብሪካው መገንባቱን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ቀይ መስቀል ማህበር  ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አማኑኤል ጳውሎስ ናቸው።

ለማምረቻው የሚሆኑ ግብአቶች፣ዕውቀትና ጉልበት ከበጎ ፈቃደኞች መገኘቱንና ማህበረሰቡ እያሳየ ያለው መተባበር የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ ሄሌን ደበበ ማህበሩ በችግር ጊዜ ከህዝብና መንግስት ጎን በመሆን እያከናወነ ላለው ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ከፋብሪካው በውድ ዋጋ ገዝተው ለመጠቀም የሚቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ በማድረግ ወረርሽኙን ለመግታት የተጀመሩ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም