የህገ-መንግስት ትርጓሜ የህገ መንግስቱን መሠረታዊ መርሆች ሳይጥስ የአገርን ሉአላዊነት የሚያሥከብር ትክክለኛ አማራጭ ነው

117

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) የህገ-መንግስት ትርጓሜ የህገ መንግስቱን መሠረታዊ መርሆች ሳይጥስ የአገርን ሉአላዊነት የሚያሥከብር ትክክለኛ አማራጭ መሆኑን የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ሊቀ መንበር ተናገሩ፡፡

በኮቪድ-19 ምክንያት ምርጫው መራዘሙ ተገቢ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ነው፡፡

የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ትዕግስቱ አወል  እና የኦሮሞ  ነጻነት  ግንባር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ  በወቅታዊ ጉዳዮች  ዙሪያ  ከኢዜአ  ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በቆይታቸውም በዚህ ዓመት ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ  በኮቪድ-19 ወረርሽኝ  ምክንያት መተላለፉ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ትዕግስቱ  አወል  እንዳሉት  በዚህ ዓመት ሊካሄድ ለታሰበው አገራዊ ምርጫ መንግስትም  ይሁን  ብሔራዊ ምርጫ  ቦርድ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከኮቪድ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የህዝብ ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጠው ስለሚገባ ምርጫው እንዲራዘም መደረጉ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ከወረርሽኑ መስፋፋት ጋር ተያይዞም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫው እንደማይደረግ ካስታወቀ በኋላ መንግስት የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን ሲያፈላልግ ነበር ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ጥረት መካካል ገለልተኛ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ሃሳብ እንዲያመጡ  በማድረግ  አራት ህገ መንግስታዊ የሆኑ አማራጮች መቅረባቸውን አንስተዋል፡፡

አማራጮቹ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ለውይይት በመቅረብ የህገ መንግስት ትርጓሜ በአብዛኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ አዎንታዊ ምላሽ አግኝቶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ከቀረቡት አማራጮች መካካልም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመረጠው የህገ-መንግስት ትርጓሜ የህገ መንግስቱን መሠረታዊ መርሆች የማይጥስ እና የአገርን ሠላምና ሉአላዊነት የሚያሥከብር ትክክለኛ አማራጭ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡

የህገ መንግስት ትርጓሜው ሂደትም በህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ አማካኝነት ምሁራን፣  የህግ ባለሙያዎችና የተለያዩ አካላት እንዲወያዩበት መደረጉም እንደ ጥሩ ጎን  የሚነሣ ነው ብለዋል፡፡

ይህ የህገ መንግስት ትርጓሜ የአገርን ደህንነት በማስጠበቅ የመንግስትን ቀጣይነት  የሚያረጋግጥ  እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ  በበኩላቸው  በኮቪድ-19 ምክንያት ምርጫው መራዘሙ ተገቢ መሆኑን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አረጋግጠዋል፡፡

ወረርሽኙ እስኪወገድና ምርጫው እንዲቆይና የሚካሄድበትን ጊዜም ጭምር በአማራጭ ለመንግስት ማቅረባቸውን አስታውቀዋል፡፡

ምርጫው ከተካሄደ በኋላም በተለመደው ሁኔታ ሰላማዊ የስልጣን ርክክብ መደረግ እንዳለበት አቶ ቀጄላ ተናግረዋል፡፡  

የህገ መንግስት ትርጓሜ ለመስጠት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የህግና ምርምር ተቋማት፣  የህገ መንግስት ባለሙያዎች፣ ህገ መንግስት በማርቀቅ አስተዋጽኦ  የነበራቸው  ባለሙያዎችና  የህግ ባለሙያዎች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ሃሳብ  የማሰባሰብ  ተግባር እየተካሄደ ነው።

ሂደቱ የህገ መንግስት ትርጉም የአተረጓጎም ጥበብን ከማሳደግ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ህገ መንግስታዊ ስርዓት እንዲሰርጽ ልዩ አጋጣሚን የሚፈጥር መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም