በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለኤዥያ ፓስፊክና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አምባሳደሮች ገለጻ ተደረገ

80

አዲስ አበባ፣ ግንብት 12/2012 (ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የኤዥያ ፓስፊክና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አምባሳደሮች ገለጻ ተደረገላቸው።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከውኃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የኤዥያ ፓስፊክና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አምባሳደሮች ስለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ገለጻ አድርጓል።

ገለጻው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንደርጋቸውና በኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው መሰጠቱን ሚኒስቴሩ ካወጣው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

የገለጻው ዋና ዓላማ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት እንዲሁም በግድቡ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶች ያሉበትን ደረጃ በተመለከተ አምባሳደሮቹ ወቅታዊ መረጃ እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለመ ነው።

የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ ድጋፍ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን እና ኃይል ለማመንጨት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ፤ ግድቡ ለኢትዮጵያ፣ ለቀጠናው ብሎም ለአፍሪካ አህጉር የሚኖረውን ጠቀሜታ በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ መሰጠቱ ተገልጿል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በትብብር፣ በፍሐዊነትና በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ ኢትዮጵያ እየገነባች መሆኑ ለአምባሳደሮቹ ተብራርቶላቸዋል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በርካታ ውይይቶችን ማድረጋቸውንና የነበሩ ልዩነቶችን በውይይት እየፈቱ ከዚህ ደረጃ መድረሳቸውን፤ በቀጣይ የሚኖሩ ልዩነቶችንም በተመሣሣይ በሦስቱ አገሮች በሚደረጉ ውይይቶች ለመፍታት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗንም ተገልጾላቸዋል።

ከገለጻው በኋላ አምባሳደሮቹ በሰጡት አስተያየት በግድቡ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች ዓለም አቀፍ መርህን በተከተለ መልኩ በውይይትና በድርድር እንደሚፈቱ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በትናንትናው ዕለትም መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍረካ አገራት አምባሳደሮች ተመሳሳይ ማብራሪያ መሰጠቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም