'የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን በቴክኖሎጂ አስደግፎ ማስቀጠል ውዴታ ሳይሆን፤ ግዴታ ነው''- ፕሮፌሰር ሒሩት

76

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) ''የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን በቴክኖሎጂ አስደግፎ ማስቀጠል ውዴታ ሳይሆን፤ ግዴታ ነው'' ሲሉ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም ተናገሩ።

አገር አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናን በተመለከተ የቪዲዮ ውይይት ተካሂዷል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአገር አቀፍ ደረጃ እያስከተለ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት በቴክኖሎጂ ታግዘው የመማር ማስተማር ሂደቱን ማስቀጠል ውይይቱ ትኩረት ያደረገባቸው ጉዳዮች ናቸው።

ፕሮፌሰር ሒሩት በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ሰው እስካለ ድረስ ትምህርትና ሥልጠና ሊቋረጥ አይችልም።

ወረርሽኙ ምንም እንኳን የገጽ ለገጽ ትምህርት እንዲካሄድ ባይፈቅድም፤ በቴክኖሎጂ ትምህርትን ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ዕውቀትና ክህሎታቸውን ተጠቅመው ማኅበረሰቡ የሚጠቀምባቸው የፈጠራ ውጤቶችን እንዲያበረክቱ ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

ለዚህም ''የቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን በቴክኖሎጂ አስደግፎ ማስቀጠል ውዴታ ሳይሆን፤ ግዴታ ነው'' ብለዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ሒሩት ገለጻ በቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርትና ሥልጠናን ለማስቀጠል ግብረ ኃይል ከማቋቋም ጀምሮ ድጋፍ የሚያደርጉ አጋር አካላትም አሉ።

ከሥልጠና ፕሮግራሞች ጋር የሚመጋገቡ ቪዲዮን ጨምሮ አዳዲስ የማሰልጠኛ ግብዓቶች በማሟላት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉት አንድ ሺህ 681 የግልና የመንግሥት ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ወረርሽኙን በመከላከል በኩል ኅብረተሰቡን የማስተማርና የፈጠራ ውጤቶችን ተደራሽ በማድረግ ድርሻቸውን እንዲወጡ ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።

ለዚህ ደግሞ የፈጠራ ሥራዎችን በዓይነትም በመጠንም በመጨመር ተደራሽ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከንክኪ ነፃ የእጅ መታጠቢያዎች፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች እያመረቱ ለአካባቢያቸው ማኅበረሰብ እያሰራጩ ይገኛሉ።

በቪዲዮ ውይይቱ የፌዴራልና የክልል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም