የአፍሪካ ኅብረት የኮቪድ-19 ለመከላከል በያዘው ጥረት እንግሊዝ አብራ ለመሥራት መዘጋጀቷን አስታወቀች

73

አዲስ አበባ ፣ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ ኅብረት ለጀመረው "የአፍሪካ ኅብረት ኮቪድ 19 ምላሽ መስጫ ፈንድ" የእንግሊዝ መንግሥት የ20 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑ ተገልጿል።

ድጋፉ የአፍሪካ መሪዎችና ቴክኒካል ኤክስፐርቶች የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በመግታት የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የሚያደርጉትን ጥረት ያግዛል ተብሏል።

በአፍሪካ በሚገኙ በርካታ አገራት በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት ካለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ዝቅተኛነት ጋር ተዳምሮ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን ይችላል ተብሏል።

ኤች.አይ.ቪን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት መቀዛቀዝ፣ የተመጣጠነ የምግብ እጥረትና ተያያዥ በሽታዎች የቫይረሱን ጉዳት አስከፊ ሊያደርጉት እንደሚችልም ተመልክቷል።

ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ሁለት ዶክተር ለ10 ሺህ ሰዎች መድረሱ ሥጋቱን ከፍ አድርጎታል።

የጤና አገልግሎቱ ደካማ ከሆነ የቫይረሱን ሥርጭት መግታት አዳጋች በመሆኑ ድጋሚ ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችልም ተጠቁሟል።

የእንግሊዝ መንግሥት ያደረገው ድጋፍ አፍሪካ ወረርሽኙን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ለማጠናከር፣ በአህጉሪቱ ያለውን የጤና ሥርዓት ለማዘመንና የአፍሪካውያንን ሕይወት ለመታደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተገልጿል።

በአህጉሩ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በሥልጠና ራሳቸውን እንዲያበቁ ማድረግ በድጋፉ ተካቷል።

ድጋፉ የጤና ባለሙያዎችን መመልመልና ከፍተኛ ተጋላጭነት ባለባቸው አካባቢዎች ማሰማራት፣ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የሚወጡ የተሳሳቱ መረጃዎችን መከላከል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ማጠናከርና የጤና ባለሙያዎች ስለቫይረሱ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ ማሰልጠን ላይ እንደሚውል ለኢዜአ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።    

ከዚህ ባሻገርም ዜጎች የኮቪድ 19 መረጃዎች በተሻለ መንገድ ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ ሌላው የፈንዱ ዓላማ ሲሆን በዚህ በኩል የእንግሊዝ መንግሥት ድጋፍ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ነው የገለጸው።  

የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ልማት ዋና  ፀሐፊ አኒ ማሪያ ትሬቭሊያን፤ ''ሁላችንም ደህና ካልሆንን ማናችንም ደህና መሆን አንችልም'' በማለት አፍሪካን መደገፍ ለእንግሊዝም ለዓለም ጤናም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።  

በአፍሪካ አገራት ውስጥ በሚገኙ የልማት አጋሮች በኩል ቫይረሱን ለመቆጣጠር እንግሊዝ ድጋፍ እያደረገች እንደሆነም አስታውቃለች።

የእንግሊዝ መንግሥት ይህንን ድጋፍ ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኮሮናን ለመከላከል እንዲረዳ 935 ሚሊዮን ዶላር መለገሷ ይፋ ሆኗል።    

የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በቫይረሱ ምክንያት በአፍሪካ 300 ሺህ ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን ሊያጡ ይችላል ሲል ማስጠንቀቁ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም