በዞኑ ጥቅም ላይ ከዋለው አሲዳማ መሬት የተገኘውን መልካም ተሞክሮ ለማስፋፋት እየተሰራ ነው

70
አምቦ ሰኔ 28/2010 በምዕራብ ሸዋ ዞን አሲዳማ መሬትን ጥቅም ላይ በማዋል የተገኘውን መልካም ተሞክሮ ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን  የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ  ሀብት  ጽህፈት ቤት ገለጸ። በሁለት ወረዳዎች ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ  በሙከራ ደረጃ 10 ሺህ 50 ኩንታል ኖራ በመጠቀም 450 ሔክታር መሬትን   በማከም  በተለያዩ  ሰብል ማልማት ተችሏል። ከዚህ በፊት ጥቅም ሳይሰጥ የቆየው ይሄው መሬት በመልማቱም 100 አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን በጽህፈት  ቤቱ የአፈር  ለምነት  ስራ ባለሙያ  ወይዘሮ  ዓለምፀሐይ  ቀቀባ ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል በሄክታር ሁለት ኩንታል ምርት ብቻ ይሰጥ የነበረ አሲዳማ መሬት በኖራ በመታከሙ ምርታማነቱ  በሄክታር በአማካይ  ከ10 ኩንታል በላይ ማደጉን አመልክተዋል። ባለሙያዋ እንዳሉት አንድ ጊዜ በኖራ የታከመ አሲዳማ መሬት  ለአምስት  ዓመት ያለምንም ተጨማሪ ኖራ ለምነቱንና  ምርታማነቱን  ጠብቆ  ምርት ይሰጣል። በሙከራ ደረጃ የተጀመረው ስራ  ውጤታማ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ወደ ሌሎች ዘጠኝ ወረዳዎች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዞኑ አሲዳማ መሬትን በማከም ወደ ምርት መመለስ ከተቻለባቸው መካከል የደንዲ ወረዳ አርሶ አደር  ሚሬሳ  ፊጡማ በሰጡት አስተያየት  አንድ  ሄክታር አሲዳማ መሬታቸው ምርት ሳይሰጥ ለዓመታት መቆየቱን አስታውሰዋል። በግብርና ባለሙያ ምክር ታግዝው ማሳቸውን በኖራ በማከማቸው አምና በሄክታር 11 ኩንታል ስንዴ ማምረት ችለዋል። የጀልዱ ወረዳ አርሶ አደር ለቺሳ ነገዎ በበኩላቸው በ2010/2011 ምርት ዘመን ግማሽ  ሄክታር አሲዳማ ማሳቸውን  በኖራ  በማከም የገብስ ሰብል መዝራታቸውንና ከቀድሞ  የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል። "አሲዳማ የሆነውን የእርሻ ይዞታዬ ምርት አልሰጥ እያለ ቢያስቸግረኝ በኖራ በማከም የዘራሁት የባቄላ ሰብል አምና ጥሩ ምርት ስላስገኘልኝ ልማቱን በሌሎች ሰብሎች ለማስፋፋት ዘንድሮ  ተነሳስቼያለሁ" ያሉት ደግሞ የኤጀርሰለፎ ወረዳ አርሶ አደር ተስፋዬ አለሙ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም