በሰሜን ሸዋ የተሻሻሉ የሙዝ ዝርያዎችን እያለሙ ያሉ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል

144
ደብረ ብርሃን ሰኔ28/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተሻሻሉ የሙዝ ዝርያዎችን እያለሙ ያሉ አርሶ አደሮች በዓመት እስከ 60 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናገሩ። የደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል በኤፍራታና ግድም ወረዳ በአርሶ አደሮች ማሳ ያላመደው የሙዝ ዝርያ በሄክታር 480 ኩንታል ምርት መስጠት አስችሏል። በቀወት ወረዳ የሌንና ዋጮ ቀበሌ አርሶ አደር ከበደ በላቸው ለኢዜአ እንደገለጹት ቀደም ሲል ውሃ ገብ መሬታቸውን በመጠቀም ሽንኩርትና መሰል አትክልቶችን ሲያለሙ ቆይተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከምርምር የወጡ የተሻሻሉ የሙዝ ዝርያዎችን በመጠቀምና የባለሙያን ምክረ ሀሳብ በመተግበር በአንድ ሄክታር መሬት ላይ የሙዝ ተክል የማልማት ሥራ መጀመራቸውን ገልፀዋል። ከሙዝ ምርት ሽያጭም በዓመት ከ60 ሺህ ብር በላይ ማግኘታቸውንና ቀደም ሲል ከአትክልት ያገኙት ከነበረው ገቢ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል። ከልማቱ ጎን ለጎንም የተሻሻሉ የሙዝ ችግኞችን አፍልተው እየሸጡ መሆናቸውን የገለጹት። አቶ ታደሰ ማንያዘዋል የተባሉ አርሶአደር በበኩላቸው በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በሩብ ሄክታር መሬታቸው ላይ 150 እግር ሙዝ ተክለው በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩ ጠቁመዋል። ከሚያገኙት ምርትም በዓመት እስከ 20 ሺህ ብር ድረስ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ነው የተናገሩት። በተያዘው የመኸር እርሻም የደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል ያወጣውን አዲስ ዝርያ ለማስፋፋት 200 እግር ሙዝ ለመትከል ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። በደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል የግብርና ምጣኔ ሀብት ተመራማሪና የቴክኖሎጂ ሽግግር አስተባባሪ አቶ አብሮ ጥጋቤ በበኩላቸው ከማዕከሉ በምርምር የተገኙና ለአየር ንብረቱ ተስማሚ የሆኑ 4 የሙዝ ዝርያዎች ለአርሶ አደሮች እየተሰራጩ መሆናቸውን ገልጸዋል። እንደ አስተባባሪው ገለጻ ቀደም ሲል በአካባቢው የነበሩ የሙዝ ዝርያዎች በሄክታር 260 ኩንታል የሚሰጡና በቀላሉ ለበሽታ የሚጋለጡ ናቸው። የአርሶ አደሩን ችግር ለመፍታት በተደረገ ምርምርም ግራንዲ፣ ናይን ጃይንት፣ ካቬደሽና ፓዮ የተባሉ የሙዝ ዝርያዎችን በማውጣት በሙከራ ደረጃ ውጤታማ በመሆናቸው ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። አቶ እብሮ እንዳሉት የሙዝ ዝርያዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለምርት ከመድረሳቸውም በላይ የአካባቢውን የአየር ንብረት ተላምደው በሄክታር 480 ኩንታል መስጠት የሚችሉ ናቸው። ይህም የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ የአካባቢውን ገበያ ለመሸፈን የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል። በተያዘው የክረምት ወራትም በአርሶ አደሩ ቋሚ የአትክልት ቦታ በስፋት እንዲተከሉ በአሁኑ ወቅት 3 ሺህ ችግኝ ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በዞኑ በሙዝ ልማት በግልና በክላስተር የተደራጁ ከ56 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን በተያዘው ዓመትም ከ131 ሺህ 788 ኩንታል በላይ ሙዝ ተመርቶ ለአካባቢው ገበያ መቅረቡ ታውቋል። የዞኑ ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ውሃ አጠቃቀም ቡድን መሪ ወይዘሮ አስካለ ይፍሩ በበኩላቸው በሰሜን ሸዋ ዞን በተያዘው የክረምት ወራት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን  ገልፀዋል። ሙዝ፣ አቦካዶ፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ ሎሚና መሰል ተክሎችን ለመትከል 1 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ለተከላ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን እስካሁን ድረስ 10 ሺህ ሄክታር መሬት በቋሚ አትክልትና ፍራፍሬ ለምቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም