ከባንኮች በጥሬ ገንዘብ ወጪ የሚደረግ ብር ላይ ገደብ ተጣለ

94

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2012 (ኢዜአ) ከባንኮች በጥሬ ገንዘብ ወጪ የሚደረግ ብር ላይ ገደብ የሚጥል መመሪያ ማውጣቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

ባንኩ ዛሬ በአዳዲስ መመሪያዎችና አተገባበር ዙሪያ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

የባንኩ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እንዳሉት፤ ከባንኮች በጥሬ ገንዘብ የሚወጣ ተንቀሳቃሽ ብር ገደብ የሌለውና ለተለያዩ ወንጀሎችና ለህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውወር የተጋለጠ ነበር።

ይህንንም ለመከላከል በጥሬ ብር የሚወጣው ገንዘብ ላይ ገደብ እንዲጣል መደረጉን ገልጸዋል።

ይህንን ችግር ለመፍታት ባንኩ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ አዲስ መመሪያ አዘጋጅቷል ብለዋል።

በዚህም በግለሰብ ደረጃ በቀን እስከ 200 ሺህ  ብር፣ በወር ደግሞ እስከ 1 ሚሊዮን ብር፣ በኩባንያ ደረጃ በቀን እስከ 300 ሺህ ብር፣ በወር እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ብቻ ማውጣት እንደሚቻል ነው የገለጹት።

ከዚህ ውጭ ክፍያዎችን መፈጸም የሚችሉት ከአካውንት ወደ አካውንት፣ በቼክና በሲፒኦ እንዲሁም በሌሎች በኤሌክትሮኒክስ አማራጮች ብቻ ነው።

የመመሪያው አስፈላጊነትም ወንጀሎችንና የግብር ስወራን ለመከላከልና ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቀነስ ነውም ብለዋል።

በማብራራያቸውም በቅርቡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በህገ-ወጥ መንገድ ሊወጣ የነበረውን 60 ሚሊዮን ብር  በምሳሌነት አንስተዋል።

መመሪያው የባንኮች የገንዘብ አከፋፈል ወደ ዘመናዊ አሰራር ለመለወጥ እንደሚረዳ አመልክተው፤ ''የመመሪያው ዋና ዓላማ የሰዎች ገንዘባቸውን የመጠቀም መብትን መገደብ ሳይሆን በአከፋፈሉ ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ያለመ ነው'' ብለዋል።

በልዩ ሁኔታ ለተፈቀደላቸው ግለሰቦችና ባንኮች ዝርዝር መመሪያ መዘጋጀቱንም ነው ገዥው የጠቆሙት።

ባንኮችም ከተፈቀደው የገንዘብ መጠን በላይ ከፍለው ሲገኙ ልዩነቱን 25 በመቶ ቅጣት እንደሚከፍሉ ነው ዶክተር ይናገር የገለጹት።

በአከፋፈል ስርዓቱ ላይ ቅደመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ከባንክ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል።

ይህ የአከፋፈል ስርዓት በብዙ አገሮች ላይ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር ባለሃብቶች አዲስ እንደማይሆንባቸውም ጠቁመዋል።

የባንኩ ገዥ በተቋሙ ከሁለት ዓመት ጀምሮ እየተሰራ ስላለው የሪፎርም ስራ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተደረጉ የሪፎርም ስራዎችም በርካታ ጥቅሞች መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም