የህገ-መንግስት ትርጓሜው አሁን ያጋጠመውን ችግር ከማለፍ ባሻገር ለቀጣይ የተሟላ ህጋዊ ሰነድ እንዲኖር ያስችላል

93

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2012 (ኢዜአ)የህገ-መንግስት ትርጉም አሁን የገጠመውን ችግር ከማለፍ ባሻገር ለቀጣይ ተመሳሳይ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መሰረት የሚጥል መሆኑን የፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት አባላት ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረትና የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ደረጀ በቀለ እንዲሁም የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ሊቀመንበርና የጥምረቱ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግር አኳያ፣ መንግሥት እየሄደባቸው ያሉት አማራጮች ህጋዊና የሚያሳምኑ ናቸው።

በመንግስትም ይሁን በተለያዩ ፓርቲዎች የመፍትሄ ሃሳቦች መቅረባቸው ዴሞክራሲያዊና ትክክለኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረትና የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ደረጀ በቀለናየኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ሊቀመንበርና የጥምረቱ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ እና አሁን ከገጠሙት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንፃር በተለያዩ አካላት የሚቀርቡት ምርጫን የማካሄድ፣ የሽግግር መንግስት የማቋቋምና መሰል ሃሳቦች ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ አለመሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በተለይም በዚህ ወቅት ህዝቡን ለምርጫ እንዲወጣ በማድረግ ለወረርሽኙ ተላጭ ማድረግ ወንጀል መሆኑን ጠቁመዋል።

በህገ-መንግስቱ በግልፅ ያልተቀመጡ ጉዳዮችን፣ የህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ  አምኖበት በትክክለኛው መንገድና ለትርጉም እንዲያመች ተደርጎ ማቅረቡ ህጋዊ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ ምሁራን፣ የህግ ባለሙያዎችና የተለያዩ አካላት እንዲወያዩበት ማድረጉ የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደዚህ አይነት አንቀፆች በትርጉም ግልፅ እየሆኑ መሄዳቸው ወቅታዊ ችግሮችን ከማለፍ ባሻገር ተመሳሳይ ችግሮችን መፍታት የሚችል ህጋዊ ሰነድ እንዲኖር መሰረት እንደሚጥልም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረትና የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ደረጀ በቀለ

"ህጉ ዝም ሲል በባለሙያዎቹ እሳቤ ትርጉም እንዲፈለግለት ነው ያስቀመጡት እንጂ ዝም ብሎ ዝም ብሏልና ዝም እንበለው የሚል አይደለም።'' ቤለዋል'።

 "ህገ-መንግስትን የማሻሻል ስርአታችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለኛ ቢሆንም ጥሩ ጅምር ይሆናል''የሚሉት የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ሊቀመንበርና የጥምረቱ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ።

የህገ መንግስት ትርጓሜ  ለመስጠት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የህግና ምርምር ተቋማት፣ የህገ መንግስት ባለሙያዎች፣ ህገ መንግስት በማርቀቅ አስተዋጽኦ የነበራቸው ባለሙያዎችና የህግ ባለሙያዎች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ሃሳብ የማሰባሰብ ተግባር እየተካሄደ ነው።

ሂደቱ የህግ መንግስት ትርጉም የአተረጓጎም ጥበብን ከማሳደግ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ህገ መንግስታዊ ስርዓት እንዲሰርጽ ልዩ አጋጣሚን የሚፈጥር መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም