ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን የዲፕሎማሲ ሥራ እንደምታጠናክር አስታወቀች

88

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የምትሰራውን የዲፕሎማሲ ስራ እንደምታጠናክር አስታወቀች።

መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍሪካ አገሮች አምባሳደሮች ዛሬ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ለአምባሳደሮቹ ገለጻ ያደረጉት የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ግድቡ ያለበትን ደረጃ፣ በቀጣይ ሀምሌ በሚጀመረው የውሃ ሙሌት ላይ እና በተፋሰሱ አገሮች ሲደረጉ የነበሩ የድርድር ሂደቶች ላይ ማብራሪያ እንደተሰጠ ተናግረዋል።

ከውይይቱ በኋላ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ በድርድሩ ሂደት የገጠሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ላይ በተመለከተ ማብራሪያ ለአምባሳደሮቹ ተሰጥቷል።

በተጨማሪም የሃይድሮሊክ ኢነርጂ ማመንጨት ለከባቢው ብሎም ለአፍሪካ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች በዝርዝር ማብራራታቸውን አንስተዋል።

ግብጽ አሁን ባለችበት ደረጃ ከኢትዮጵያ 10 እጥፍ ሀይል የማመንጨት አቅም ያላት መሆኑን አንስተው፤ ኢትዮጵያ ሀይል ለማመንጨት የሚያስችላት ውስን ሀብት ብቻ እንዳላት ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ 86 በመቶ ከራሷ የሚመነጨውን ውሃ የመጠቀም መብት እንዳላት ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ በየትኛውም አገር ላይ ተጽዕኖ እንደማያደርስም ጠቁመዋል።

የውሃ የመጠቀም መብት ለሁሉም መሆን እንዳለበት እና ኢትዮጵያ የሌለችበት የቅኝ ገዢዎች ስምምነት በምንም መልኩ ተቀባይነት እንደሌለው በማንሳት በፍትሃዊነት የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ነው ያብራሩት።

በመጨረሻም በግድቡ ዙሪያ የሚደረገው የዲፕሎማሲ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ማብራሪያውም በቀጣይነት ለመካከለኛው ምስራቅ፣ አውሮፓና እሲያ አገሮች እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው የሚገነባው ግድብ ብርሃን ከመስጠት አልፎ የዜጎችን ህይወት የሚቀይር መሆኑን ሁሉም ወገን እንዲያውቀው የዲፕሎማሲ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በየትኛውም አገር ላይ ተጽዕኖ የማያሳድር መሆኑን የተናገሩት አምባሳደር ሬድዋን፤ ''ይሄንን እውነታ በተጨባጭ መረጃ እያደረሱ ለዓለም ማሳወቅ ይገባል'' ብለዋል።

ግድቡ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከጎረቤት አገሮች አልፎ አፍሪካ ተያይዛ ለማደግ በምታደርገው ጥረት ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው በማንሳት፤ ይሄንን ለጎረቤት አገሮችም ሆነ ለሌሎች አገሮች በዲፕሎማሲ የማሳወቅ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አሁናዊ ክንውኑ 73 በመቶ የደረሰ ሲሆን በመጪው ክረምት ውሃ መያዝ እንደሚጀምር ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም