የፈጠራ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ ቀረበ

56

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2012 (ኢዜአ) የገጠመንን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለማለፍ  ሀብታችንንና ዕምቅ አቅማችንን   አቀናጅተን መጠቀም አለብን  ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስ ቡክ ገጻቸው ‹‹ብዙዎቹ የፈጠራ ውጤቶች የፈተና ልጆች ናቸው›› ይባላል ሲሉም ሰፊ ሐተታ አቅርበዋል።

`አንጡራ ሀብት` የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ያገኘው የሚታይና የማይታይ ሀብት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ `ዕምቅ ዐቅም` ደግሞ የሰው ልጅ ያለው አእምሯዊ አቅም በመሆኑ

ይህ አእምሯዊ አቅም ይበለጠ በተፈተነ ቁጥር የበለጠ ጥቅም ላይ ይውላል ብለዋል።

እኛ ኢትዮጵያውያን ከኮቪድ 19 በኋላ እጅግ የተሻለችና ፈተናውን በድል ያለፈች ሀገር ለማየት ከፈለግን እነዚህ ሦስቱን አቅሞቻችንን አጣምረን መጠቀም የግድ ይለናል ይላሉ ዶክተር ዐብይ  ።

እያንዳንዷን ሀብት በሚገባ መፈተሽና ያለ ብክነት መጠቀም አለብን የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀብትን የሚያበዛው የተገኘው መጠን ብቻ ሳይሆን የአጠቃቀም ችሎታውም እንደሆነ በማስረዳት።

እንደ ሀገር ሀብትን መልሶ ጥቅም ላይ የማወል አቅምና ጥበብን በየጊዜው ማሳደግ ተገቢነቱ አያጠያይቅም ያሉት ዶክተር ዐብይ፤ ለዚህም ሕብረተሰባችንን በማስተማርና ንቃተ ህሊናው እንዲዳብር በመትጋት በኩል ሁላችንም ሀላፊነት አለብን ሲሉ አሳስበዋል።

ትልቁ የሰው ልጆች የሀብት ምንጭ አዕምሮ እንደመሆኑ መጠን፣ እውቀት ላይ የተመሰረቱ ሀብቶቻችንን አብዝተን ለመጠቀም ከፍተኛ ትግል ከማድረግ መቦዘን የለብንም ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የማይነጥፈውን የሀብት ምንጭ አዕምሮን ወደ ሀብትነት የምንቀይርበት ዋነኛው መንገድም ፈጠራ ነው የሚሉት ዶክተር ዐብይ፤ `ፈጠራዎች` ችግር ፈቺ፣ ወጪ ቆጣቢ እና በርካሽ ዋጋ ለብዙዎች ተደራሽ መሆን ሲችሉ ሀገር ከፈጠራዎቹ የምታገኘው ጥቅም በጣም ከፍተኛ ይሆናል።

ለዚህም፣ ደግሞ ደጋግሞ ማሰብ በእጅጉ ይጠይቃልም ብለዋል።

ኮቪድ 19`ን ተከላክለን የተሻለች ሀገር ለመገንባት ባለን ሀብት ላይ እውቀትና ፈጠራን አቀናጅተን መጠቀም ይኖርብናል ሲሉ 

በዚህም ፋታ የማይሰጠውን ወረርሽኝ ፋታ ልንነሣው እንችላለን ሲሉም ጠቁመዋል ።

በአሁኑ ወቅት፥ በገጠርና በከተማ የሚገኙ ለእርሻ ምቹ የሆኑ መሬቶቻችንን ለምግብ ሰብል ምርት ማዋል አለብን የሚሉት ዶክተር ዐብይ፤ አምራች ኢንዱስትሪውና ሠራተኞቹ ዐቅማቸውን ሁሉ ለተጨማሪ ምርት እንዲያውሉ ማበርታት ይገባናል ሲሉም አሳስበዋል።

በግብርና ሥራ ላይ የተሠማሩ አርሶ አደሮችና ባለሞያዎችን ማበረታታት ተገቢ ነው መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመጭው ክረምት ያቀድነውን የ5 ቢልዮን ችግኝ ተከላ ወገባችንን አሥረን ማሳካት እንዳለብን 

ገልጸዋል።

በተጨማሪም ዜጎች በቤት ሲቀመጡ ሊያከናውኗቸው የሚገቡ የሞያና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በትጋት ከማከናወን ባለፈ የሀገር ፍቅርና የሕዝቦች አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በዚህ መልኩ ለወረርሽኙ ስርጭት እድል ሳንፈጥር ለሀገር ግንባታ ከተጋን ያለ ጥርጥር ኮሮናም በቀላሉ ይሸነፋል፤ ሀገራችንም በብልጽግና ጎዳና ትረማመዳለች ብለዋል ዶክተር ዐብይ።

ለዚህ ደግሞ የቴክኖሎጂና የኪነ ጥበብ ፈጠራዎች የበለጠ ጉልበት እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የማኅበረሰቡን አስተሳሰብ የሚያሳድጉና ፈተናን ወደ ዕድል የሚቀይሩ አብሪ ሐሳቦች በተለይ በዚህ ወቅት በእጅጉ እንደሚያስፈልጉ አሳስበዋል።

ስለሆነም መንግስት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የሕዝቡን ኖሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂና የኪነ ጥበብ ፈጠራ ያሏቸውን ኢትዮጵያውያን ማበረታታት እንደሚፈልግ ያሳወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ።

ከዚህ አኳያ፡-የገበሬውን ምርታማነት ሊያሻሽሉ የሚችሉ አዳዲስ አሰራርና ቴክኖሎጂዎች፣ የከተማ ግብርናን የሚያበረታቱና ውጤታማ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ዘዴዎች አስፈለጊ እንደሆኑ አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የፋብሪካ ምርታማንትን የሚያሳድጉ አሰራሮች፣ዜጎቻችን በቤት ውስጥ ሲቀመጡ የንባብ ፍላጎታቸውና ችሎታቸው እንዲዳብር የሚያደርጉ ፈጠራዎች፣  ማራኪ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች፣ሕዝቡን ለፈጠራ፣ የቴክኒክ እውቀትን ከፍ ለማድረግ የሚረዱ ድርሰቶች፣ ሙዚቃዎች፣ ሥዕሎች፣ አጫጭር ድራማዎችና አጫጭር ፊልሞች በእጅጉ ያስፈልጋሉሜ ብለዋል።

 የሕዝብ አንድነት፣ የእርስ በርስ ትውውቅና የሀገር ፍቅር ስሜት የሚያሳድጉ ጥበቦችና ፈጠራዎች ያሏችሁ ሳትዘገዩ አውጧቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በዚህ መልኩ እስከ መስከረም ድረስ በተለያዩ ሚዲያዎችና መድረኮች የሚቀርቡ የተሻሉ የፈጠራ ውጤቶችን መርጦ በቀጣዩ ዓመት ለመሸለም በመንግስት በኩል ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገም ገልጸዋል።

ሥራዎቻችሁን  በማህበራዊ ሚዲያዎች  የማስተዋወቂያው ትክክለኛ ጊዜ አሁን ነው የሚሉት ዶክተር አብይ ይሄንንም ተከታትሎ የሚይዝና ከየሚዲያው ወስዶ በመመዝገብ ለሽልማት የሚያጭ አካል መንግሥት በቅርቡ እንደሚቋቋም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም