ሕገ መንግሥቱን መሠረታዊ መርሆዎቹንና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ መተርጎም ይገባል - ምሁራን

75

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ምክንያት የተራዘመው ምርጫ ያስከተለውን ቀውስ ለመፍታት የሕገ መንግሥቱን መሠረታዊ መርሆዎችና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ መተርጎም እንደሚገባ ተገለጸ።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምርጫ እንዲራዘም ከማስገደድም ባለፈ በአገሮች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበለት የትርጉም ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከባለሙያዎች፣ ከምሁራንና ከሕገ መንግሥቱ አርቃቂዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

ተወያዮቹ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት አገሪቱ ምርጫን አስመልክቶ ያጋጠማትን ችግር ለመወጣት የሕገ መንግሥቱ መርሆዎችንና ነባራዊውን ሁኔታ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል።

በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሣይንስና የሕግ ምሁር ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም እንዳሉት ሕገ መንግሥት ለችግር ጊዜ አገልጋይ መሆን አለበት።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት የሕገ መንግሥቱን መሠረታዊ መርሆዎች በመረዳት መተርጎም ይገባል ብለዋል።

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት የፖለቲካና የዲሞክራሲያዊ መብቶች እንደአስፈላጊነቱ በጊዜያዊነት ይገደባሉ።

የምርጫው መራዘምም የእዚሁ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ምክንያት የተራዘመውን ምርጫ ተከትሎ ምን መደረግ እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ ግልጽ ድንጋጌ እንደሌለም አስረድተዋል።

በመሆኑም በወረርሽኙ ምክንያት ለተራዘመው ምርጫ መፍትሔ ለመስጠት ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ አድርጎ መተርጎም ያስፈልጋል ብለዋል።

የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አባል የነበሩት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በበኩላቸው "የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች በተናጠል እንደ ሰበዝ እየተነጠሉ የሚተረጎሙ አይደለም" ይላሉ።

በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ አንድን አንቀጽ ለማብራራት የሕገ መንግሥቱን አጠቃላይ መንፈስ መረዳት ተገቢ መሆኑንም አስረድተዋል።


በኢትዮጵያ የሥልጣን አወጣጥን በተናጠል ወይም በጣምራ ቅብበሎሽ ባለው በሕጋዊ መንገድ እንደሚከናወን ያስረዱት አምባሳደር ታዬ፤ የሥልጣን ሽግግር ሕገ-መንግሥታዊ በሆነ በምርጫ ብቻ እንደሚሸጋጋር በሕገ መንግሥት በግልጽ ተቀምጧል ብለዋል።


በተለይም የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9 በተቻለ መጠን የሥልጣን ክፍተት እንዳይኖር የሚያደርጉ አንቀጾች እንዳሉትም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ጉዳዩች ያልተጠበቁ በመሆናቸው አገርን ለማስቀጠልና የፖለቲካ መረጋጋትን ለማምጣት ማሰብ አንደሚገባም አምባሳደር ታዬ አሳስበዋል።

ሌላው የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አባል የነበሩት አምባሳደር አብዱልአዚዝ መሐመድ፤ ሕገ መንግሥቱ ችግር ሲፈጠር ትርጉምም መስጠት እንደሚቻል በግልጽ አስቀምጧል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ሰዎች የሕገ መንግሥት ትርጉም አስተያየት ከመስጠታቸው በፊት ሕገ መንግሥቱ የጸደቀበትን ወቅት ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ያለው አካልም የሕገ መንግሥቱን መርሆዎች ታሳቢ አድርጎ መፍትሔ መፈለግ አለባቸው ብለዋል።

ሕገ-መንግሥቱ በሚረቀቅበት ወቅት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት በአንድ ወገን ምርጫ ይካሄድ በአንድ ወገን ደግሞ ምርጫ መካሄድ የለበትም የሚል ክርክር ተነስቶ የነበረ ቢሆንም፤ ብዙም ውይይት ሳይደረግበት መታለፉን አስታውሰዋል።

በወቅቱ በመንግሥት ላይ የሥልጣን ክፍተት ቢከሰትና አገሪቱ ያለ መንግሥት እንዳትቆይ ምን መደረግ አለበት በሚል ራሱን የቻለ ውይይት ባይደረግም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ አስገዳጅ ሁኔታ ቢፈጠርና እንደ አሁኑ ምርጫ ማድረግ ባይቻል የምርጫ ዘመናቸው ያበቃ አካላት ጉዳይ ላይ ሀሳብ እንዳልተንሸራሸረም አምባሳደር አብዱልዚዝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም