በኮቪድ 19 ምክንያት የተራዘመውን ምርጫ በሚመለከት የመንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ውይይት ቀጣይነት ያስፈልጋል

108

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10/2012(ኢዜአ) በኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ የጤና ሥጋት ምክንያት የተራዘመውን ምርጫ በሚመለከት መንግሥትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጣይ ውይይቶችን ማድረግ እንዳለባቸው ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ ተናገሩ።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የባለሙያዎችን አስተያየት በማሰባሰብ ላይ ይገኛል።

የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የመንግሥት አማካሪ የነበሩት ፕሮፌሰር አንድሪያሰ እሸቴ ዛሬም በቀጠለው ውይይት ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ያለች አገር በተለይም የምርጫ ጊዜ በተቃረበበት ወቅት በምን መልኩ ሂደቱ ሊከናወን ይገባል የሚል ጥያቄ ከጉባዔው አባላት ተነስቷል።

ለዚህ ጥያቄም ፕሮፌሰር አንድሪያስ ሲያብራሩ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ቀጣይ ውይይት ማድረግ እንዳለበት አመላክተዋል።

በተለይም በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የምርጫ ሂደት ምን መሆን እንዳለበት ያስቀመጠው ነገር አለመኖሩ ክፍተት መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም ወረርሽኙ የሚገታበት ጊዜ ወይንም መድኃኒትና ክትባት ባለመታወቁ የዘንድሮውን ምርጫ ለማካሄድም ሆነ በጊዜ ገደብ ለማራዘም አዳጋች ይሆናል ብለዋል።

በመሆኑም ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የምርጫውን ሂደት በሚመለከት ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ መተማመን ላይ ቢደርስ የተሻለ ነው የሚል ሀሳብ ፕሮፌሰር አንድሪያስ አንስተዋል።

በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አስተባባሪነት በሕገ መንግሥት ትርጉም ላይ የባለሙያዎችን ሀሳብ ለመስማት የተዘጋጀው መድረክ በጥያቄና በምሁራን ማብራሪያ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም