በትግራይ ማእከላዊ ዞን የመስኖ ምርት ገበያውን እያረጋጋ ነው

43

አክሱም ግንቦት10/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) - በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ከመስኖ ልማት የተገኘው አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ገበያውን በማረጋጋት ገንቢ ሚና መጫወቱን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።

በመስኖ ልማት የተሳተፉ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለኅብረት ሥራ ማኅበራትና  በተደራጀ መልኩ ለነጋዴዎች በማቅረብ የገበያ ትሥሥር እንዲፈጠር መደረጉን የዞኑ አስተዳደር ገልጿል።  

በዞኑ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የመስኖ ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኃይለማርያም ወልደገብርዔል ለኢዜአ እንደተናገሩት በመስኖ ልማት አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እስከ አሁን ድረስ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለገበያ ማቅረብ ተችሏል ።

ከ13 ሺህ 300  ሄክታር መሬት የተሰበሰበው ምርት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት  የገበያ  ችግር  ሊያጋጥመው ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሮ የነበረ  ቢሆንም በግልባጩ  ተፈላጊነቱ ጨምሮ ለገበያ ማረጋጋት ተግባር መዋሉን አስረድተዋል።

የኅብረት ሥራ ማኅበራት የገበያ ትሥሥሩ አካል መሆናቸው አርሶ አደሩ ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝና ፍላጎትና አቅርቦት እንዲጣጣም እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል።

በቀጣይም አርሶ አደሩ የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ በዞኑ ካሉት 197 የኅብረት ሥራ ማኅበራት የገበያ ትሥሥርን ለማጠናከር መታቀዱን ባለሙያው አስረድተዋል።

በታሕታይ ማይጨው ወረዳ የሓዱሽ ዓዲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገብረእግዚአብሔር ገብርሔት በሰጡት አስተያየት ከመስኖ 12 ኩንታል ሽምብራና ሽንኩርት አምርተው ለኅብረት ሥራ ማኅበር በማቅረብ የተሻለ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በወረዳው የማይዓጽሚ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኃይላይ ሓረጎት በበኩላቸው ቫይረሱን  ከመከላከል ጎን ለጎን በመስኖ ልማት ጠንክረው በመሥራት ስምንት ኩንታል ምርት እንዳገኙና በጥሩ ዋጋ መሸጣቸውን ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም