የኮቪድ-19 ተጽእኖን ለመቀነስ ተጨማሪ 500 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው

62

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10/2012(ኢዜአ) ኮቪድ-19 በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመቀነስ በዘንድሮ መኸር በመንግስትና በግል ሰፋፊ እርሻዎች ተጨማሪ 500 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዘንድሮ የመኸር ወቅት በመደበኛ ፕሮግራም 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄከታር መሬት ለማልማት ታቅዷል።


በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮናቫይረስ በዘርፉ ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመቀነስ ተጨማሪ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በተለይ የእርሻ ቦታዎችን የማልማት ስራዎች የሚከናወን ሲሆን እነዚህም በተለያዩ አካባቢዎች በመንግስት እና በግል ባለሃብቱ ሳይታረሱ የቀሩ መሬቶችን ወደ ልማት የማስገባት ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ኢሳያስ ገለፃ በዘንድሮው መኸር ወቅት በአጠቃላይ ከ355 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት እየተሰራ ነው።


በሌላ በኩል በዚህ ዓመት 17 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የሚሰራጭ መሆኑም ታውቋል።

ከዚህ ውስጥም 3 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው ካለፈው ዓመት የምርት ዘመን የተረፈ ሲሆን 14 ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ከዚህም አብዛኛው ቀድሞ ግዥ የተፈጸመ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በመጓጓዝ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ጋር በተያያዘም በዘንድሮው መኸር መደበኛ ፕሮግራም 178 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዷል።

ከዚህ በተጨማሪም ወቅታዊ ሁኔታውን ታሳቢ በማድረግ ተጨማሪ ከታሰበው ተጨማሪ 50 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይመረታል ተብሏል።

በአጠቃላይ በመኸር ወቅቱ 229 ሚሊዮን ኩንታል አትክልትና ፍራፍሬ ለማምረት መታቀዱም ተጠቁሟል።

የኮሮናቫይረስ ከዓለም የጤና ቀውስነቱ በተጨማሪ ውስብስብና ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የዘረፉ መሁራን ይገልፃሉ።

ኮቪድ 19 በተለይ ደግሞ በዝቅተኛ ገቢ በሚተዳደሩ የዓለም ህዝቦች ላይ ጫናው በርትቶ ከ100 እስከ 150 ሚሊዮን ዝቦችን ለርሃብ ይዳርጋል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

የችግሩን አሳሳቢነት ለመቀነስ በተለይ ታዳጊ አገሮች የግብርና ምርታቸውን ማሳደግ እንደሚገባ ይታመናል።

ለዚህም ሲባል ኢትዮጵያ የግብርና ምርቷን ለማሳደግ እየሰራች መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም