የኢትዮ-ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቀቀ

58

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10/2012(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ እና ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቀቀ።

በሁለቱ አገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተወከለው የኢትዮጵያ-ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ ከግንቦት 8-10  በአዲስ አበባ ተገናኝቶ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው፣ በድንበር ጉዳዮች እና  አዋሳኝ አካባቢዎች የጸጥታና ደህነንት ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል።

የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድን በኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ሲሆን፤ የሱዳን የልኡካን ቡድን ደግሞ በሱዳን ሪፐብሊክ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ኦማር በሽር ማኒስ ተመርቷል።

የፖለቲካ ምክክሩ በሁለቱ አገራት መካከል መልካም ግንኙነትን፣ ሰላምን፣ አብሮ መኖርን እና በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ የረጅም ጊዜ ግንኙነቶችን በሚያጠናክር መንፈስ ተካሂዷል ተብሏል።

ውይይቱ በተለይ በሁለቱ አገራት አዋሳኝ አካባቢዎች በየጊዜው የሚያጋጥሙ የጸጥታና የደህንነት ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉና የሁለቱን አገሮች የድንበር ጉዳይ በተመለከተም የህዝቦችን አብሮነትና የግንኙነቱን ታሪካዊ ዳራ ግምት ውስጥ በማስገባት  ማስቀጠል እንደነበር የውጭ ጉዳይ ያወጣው መግለጫ ያሳያል።

በሁለቱ አገራት አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ ህገ ወጥ የሰዎችና የመሳሪያ ዝውውር፣ አፈናና የመሳሰሉ ህገ ወጥ ድርጊቶችን በጋራ ለመከላከልና መፍትሄ ለመሻት የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል።

በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ተረጋግጠው ያለምንም መስተጓጎል የእርሻ ስራቸውን መቀጠል እንዳለባቸውም መግባባት ላይ ደርሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የመጣ የደህንነት ስጋት እና የነዋሪዎችን የተረጋጋ ህይወት የሚያውኩ አዳዲስ የጸጥታ ሃይል እንቅስቃሴዎች በአፋጣኝ እንዲስተካከሉ በተደረገው ውይይት የጋራ ግንዛቤ ተይዞበታል።

የሁለቱ አገራት አጎራባች የአስተዳደር አካላትም በየጊዜው እየተገናኙ ልዩነቶችን በማጥበብ በጋራ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ መምከር እንዳለባቸውም መግባባት ላይ ተደርሷል።

ሁለቱ ወገኖች ቀጣዩን የኢትዮ-ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ በሰኔ 2012 ዓ.ም አጋማሽ በካርቱም ለማካሄድ ተስማምተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም