በድሬዳዋ በ150 ሚሊዮን ብር የተገነባው የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

112

ድሬዳዋ፣ ግንቦት10/2012 (ኢዜአ) በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ መንደር በ150 ሚሊዮን ብር የተገነባው ሶዳ ኪንግ የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተመርቆ ማምረት መጀመሩን የፋብሪካው አመራሮች ገለጹ።

የፋብሪካው ዋና ሥራ አስፈጻሚና ባለድርሻ አቶ ሙሄዲን ፉክረዲን በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደገለጹት በሀገራችን በአዮዲን እጥረት የሚከሰተውን የጤና ችግር ለመቅረፍ ጨውን ከአዮዲን ጋር የሚቀላቅል ፋብሪካ ተገንብቶ ማምረት ጀምሯል።

አቶ ሙሄዲንን ጨምሮ በሦስት የድሬዳዋ ተወላጅ ባለሀብቶች የተገነባው ፋብሪካ ከጅቡቲ የባሕር ጨው በማስመጣትና በአዮዲን በማበልጸግ በተለያዩ መጠኖች ለገበያ ማቅረብ ጀምሯል።

በቀን አንድ ሺህ 50 ኩንታል ጨው የሚያቀነባብረው ይኸው ፋብሪካ ለጊዜው ለ120 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተነግሯል።

ፋብሪካው በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ ተጨማሪ የማስፋፊያ ግንባታ በማከናወን ላይ በመሆኑ የሥራ ዕድል የሚያገኙትን ዜጎች ቁጥር በእጥፍ ያሳድገዋል ብለዋል።

የፋብካው ሥራ አስኪያጅ አቶ ኑረዲን አልይ እንዳሉት ደግሞ ላለፉት ሦስት ዓመታት በግንባታ ላይ የነበረው ይኽው ፋብሪካ የማምረት ሥራውን የሚያከናውነው ሠራተኞቹን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ የሚያስችሉ ግብአቶችን በማሟላትና አስፈላጊውን የመከላከያ ዘዴዎች በመጠቀም ነው።

ፋብሪካው ተጨማሪ የለስላሳ መጠጦችና የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶችን የሚያመርቱ እህት ፋብሪካዎችን ገንብቶ እያጠናቀቀ እንደሚገኝ አያይዘው ገልጸዋል።

ፋብሪካውን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ እንደገለጹት ድሬዳዋን የምሥራቁ የሀገሪቱ ክፍል የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። 

የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካው የእዚሁ አካል መሆኑን ገልጸው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ምጣኔ ሀብት በማጎልበት ገንቢ ሚና ይጫወታል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ልዩና አስፈላጊ ድጋፍ እንደሚያደርግም ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል።

በፋብሪካው የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል ወጣት ረይስ አባቢያ በሰጠው አስተያየት "ፋብሪካው ያለ ሥራ ተቀምጠው የነበሩ በርካታ ወጣቶች ተስፋ እንዲለመልም አድርጓል። እኔም ሥራ በማግኘቴ ያቋረጥኩትን ትምህርት በመቀጠል የተሻለ ሕይወት እንደምኖር ተስፋ አለኝ" ብሏል፡፡

ሌላዋ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ወጣት ደሰቱ አብደላ በበኩሏ ሠራተኞቹ በሙሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል መሠረታዊ ጥንቃቄ እያደረጉ መሆኑን ተናግራለች፡፡

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር አፈ-ጉባዔና የካቢኔ አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም