የኢንቨስትመንት ቦታ ባለመግኘታቸው መስራት እንዳልቻሉ የአምቦ ከተማ ባለሃብቶች ገለጹ

62
አምቦ ሰኔ 28/2010 በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ለመሰማራት ቦታ ጠይቀው ምላሽ በማጣታቸው መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ የአምቦ ከተማ ባለሀብቶች ገለጹ፡፡ ከባለሀብቶቹ መካከል አቶ ደመላሽ ድሪባ ለኢዜአ እንዳሉት በከተማዋ ኮሌጅ ለመገንባት ለመጀመሪያው ዙር ስራ 50 ሚሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግበው በ2009 ዓ.ም. የመስሪያ ቦታ ጠይቀው ነበር፡፡ ሆኖም ከተማ አስተዳደር  ተመላልሰው ቢጠይቁም የቦታ አቅርቦት ችግር አለብን ከማለት ውጪ ምላሽ አጥተው መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ አመልክተዋል፡፡ ለሁለት ዓመት የጠበቁት የቦታ ምላሽ አሁን ወደ ሶስተኛ ዓመት መሸጋገሩን ጠቅሰው  ሊሰማሩበት በነበረው ዘርፍ ለ300 ሰዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር  ጭምር አስበው እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል፡፡ "በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት የሚጠበቅብኝን  አሟልቼ  የቦታ ጥያቄ ባቀርብም  በከተማ አስተዳደሩ በኩል ምንም ምላሽ አልተሰጠኝም " ያሉት ደግሞ ሌላው ባለሃብት አቶ ባጫ ደራራ ናቸው፡፡ በ40 ሚሊየን ብር ወጪ ኮንክሪት ምሶሶ ፣ በድንጋይ መፋጫ እና በብሎኬት ማምረቻ  የስራ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት የቦታ ጥያቄ ያቀረቡት ባለፈው ዓመት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም በከተማ አስተዳዳሩ በኩል የቦታ አቅርቦት ችግር እንዳለባቸው እንደተገለጸላቸው ነው ያመለከቱት፡፡ የመስሪያ ቦታ አግኝተው ወደ ስራ ሲገቡም ለ500 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ባቀረቡት የስራ እቅድ ላይ ማመላከታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ አቶ ደለሳ ቦንሳ የተባሉት ባለሀብት በበኩላቸው በከተማዋ 35 ሚሊዮን ብር ካፒታል በማስመዝገብ የዱቄት ፋብሪካ ለመገንባት በተያዘው ዓመት መጀመሪያ ላይ የስራ እቅዳቸውን ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ የከተማ አስተዳደር ግን ያቀረቡትን  የቦታ ጥያቄ እስካሁን ምላሽ እንዳልሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በአምቦ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ ቱራ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ካለፈው ዓመት ወዲህ ከ280 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በከተማዋ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት የስራ እቅድ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለሃብቶቹ በማንፋክቸሪንግ ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ፣ በኮሌጅ ግንባታና በማምረቻ ዘርፎች  ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ናቸው ፡፡ ለዚህም የስራ እቅዳቸው 15 ባለሃብቶች የከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ቦታ ባለማዘጋጀቱ ማስተናገድ እንዳልተቻለ አመልክተዋል፡፡ በከተማው አስተዳዳር የመሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምስጋና ወልደ ጊዮርጊስ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በከተማዋ በመሬት ዙሪያ በርካታ የመልካም አስተዳዳር ችግሮች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ የጥልቅ ተሃድሶ ከተካሄደ ወዲህ ክፍተቶች ተለይተው የመሬት አቅርቦቱ  ችግር  ለመፍታት  ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ በከተማዋ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ባሉት የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት  ጠያቄ ላቀረቡት ባለሃብቶች በመጪዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ የመስሪያ ቦታ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። በአምቦ ከተማ ባለፉት ዓመታት ከ900 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ያሳመዘገቡ 117 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙም ተመልክቷል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም