በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች 350 የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው

40
ነገሌ ሚያዚያ 30/2010 በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት ከአካባቢያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች በነገሌ ከተማና አካባቢው 350 የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተካሐደ ነው። የጉጂ ዞን አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት  እንዳስታወቀው ቤቶቹ እየተገነቡ ያሉት የዞኑ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች በለገሱት በ17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ነው። መኖሪያ ቤቶቹ እየተሰሩ ያሉት ተፈናቃዮቹ ለኑሮ ምቹ ነው ብለው እራሳቸው በመረጧቸው በነገሌ ቦረና ከተማና በነገሌ ዙሪያ ወረዳ አካካቢ ባሉ ቦታዎች ላይ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበበ አባጉልጉ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም በነገሌ ከተማ ለ42 ተፈናቃይ አባውራዎች የሚያገለግል የመኖሪያ ቤት ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑን ነው ያመለከቱት። ለተፈናቃዮቹ እየተሰሩ ያሉት የመኖሪያ ቤቶች እያንዳንዳቸው ባለ ሁለት ክፍል ቤቶች ሲሆኑ ቤቱ ያረፈበትን ጨምሮ አጠቃላይ ግቢው 150 ካሬ ሜትር ስፋት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ የመኖሪያ ቤቱን ለመስራትና ተፈናቃይ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣና በዞን፣ በወረዳና በከተማ አስተዳዳሪዎች የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን አመልክተዋል፡፡ የነገሌ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት ማናጅመንት ጽህፈት ቤት ከ52 ሺህ 500 ካሬ ሜትር በላይ ስፋት ያለው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ በነጻ መስጠቱንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በግጭቱ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ 810 የቤተሰብ አባላት ጉጂ ዞን ውስጥ እንዳሉ ከኃላፊው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከሱማሌ ክልል ሊበን ዞን ሱፍቱ ከተማ ከስድስት ልጆቻቸውና ከባለቤታቸው ጋር የተፈናቀሉት አቶ አደን ሁሴን ተከስቶ በነበረው ግጭት 400 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት እንደወደመባቸው ተናግረዋል። አሁን ባሉበት አካባቢ አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ መደሰታቸውንና ህዝቡ ላደረገላቸው ወገናዊ አቀባበልም ምስጋናቸውን አቅርበዋል ። ሰላም የህልውና መሰረት እንደሆነ የገለጹት አቶ አደን "ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጩ ጸረ ሰላም ኃይሎችን የኦሮሚያና የሱማሌ ክልል ህዝቦች በጋራ በመተባበር መታገል አለብን" ብለዋል፡፡ "ተከስቶ የነበረው የወሰን ግጭቱ ዜጎችን ችግር ላይ ከመጣል በስተቀር አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ የለበትም" ያሉት ደግሞ ከሊበን ዞን ታካበሌ ወረዳ ከባለቤታቸው ጋር የተፈናቀሉት አቶ ጣጦ መሊቻ ናቸው፡፡ ከተፈናቀሉ ጌዜ ጀምሮ እስካሁን በምግብ እህል ሲረዱ እንደነበር ገልጸው በአሁኑ ወቅት ለተፈናቃዮች በተጀመረው የመኖሪያ ቤት ግንባታ መደሰታቸውን ተናግረዋል ። "የእርስ በርስ ግጭት በሀገር ሰላምና ልማት ላይ ጫና ከመፍጠርና የዜጎችን ሕይወትና ንብረት ከማሳጣት የዘለለ ትርጉም ስለሌለው እርስ በርስ  በመፋቀርና በመተባበር ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎችን አደብ ልናስገዛቸው ይገባል" ብለዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም