የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቨርቸዋል ሩጫ ተካሄደ

123

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2012 (ኢኤአ) በታዋቂ አትሌቶች መሪነት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ያሳተፈ በኢንተርኔት የታገዘ የቀጥታ ቪዲዮ 'ቨርቿል ሩጫ' መርሀ ግብር ትናንት ተካሂዷል።

ሩጫው የተዘጋጀው ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የታላቁ አፍሪካ ሩጫ አስተባባሪነት ነው።

በቨርቹዋል ሩጫ መርሀ ግብሩ ላይ አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ስለሺ ስህን፣ ፋጡማ ሮባ፣ ሚሊዮን ወልዴ እና እጅጋየሁ ዲባባ ተሳትፈዋል።

በውድድሩ 1 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ከመላው ዓለም ሆነው  ዙም (Zoom) በተሰኘ መተግበሪያ ላይ በኢንተርኔት በቀጥታ እየተያዩ በቤታቸው እና ግቢያቸው ውስጥ ሆነው በመሮጥ  እና ሶምሶማ በማድረግ ተሳትፈዋል።

የውድድሩ ዋና አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አብዛ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኮቪድ-19 በሽታ በዓለም ዙሪያ ከፈጠረዉ የጤና ፈተና ጎን ለጎን፣ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጫና አስከትሏል።

ጫናው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ይሄንን ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ ለማቃለል ውድድሩ ተዘጋጅቷል።

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን በተለይ ደግሞ ወረርሽኙ በበረታባቸው አሜሪካና አውሮፓ የሚገኙ ኢትዮያዊያን ከተለመደው የአኗኗር ዘይቤ በወጣ ሁኔታ ረዘም ላለ ጊዜ ቤት ውስጥ ለመቀመጥ በመገደዳቸው ሥራን እንደ ወትሮው ወጥቶና ነፃ ሆኖ መስራት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

ይህ መሆኑ ደግሞ በበርካቶች ላይ ስጋትና የአዕምሮ ጭንቀት በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር ጋሻው፤ ጫናውን በተወሰነ ደረጃ ለመቀነስ የሚያግዝ በኢንተርኔት በቤትና ግቢ ውስጥ ሆነው የሚሮጡት የቨርቹዋል ሩጫ ተዘጋጅቶ በስኬት መከናወኑን አመልክተዋል።

አንጋፋና ብርቅዬ አትሌቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን  የተሳተፉበት፣ የኢትዮጵያ ቨርቹዋል ሩጫ ላይ መሳተፍ  መቻላቸውን ገልጸዋል።

ከዝግጅቱ የተገኘው ገቢ በኮቪድ-19 ዙሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሰሩ ሁለት መንግስታዊ ያልሆኑና በኢትዮጵያዊያን ለሚመሩ አነስተኛ ድርጅቶች የሚበረከት መሆኑንም አክለዋል።

በሩጫው ላይ አትሌቶች በያሉበት ቦታ ሆነው በቪዲዮ ተራ በተራ እየሮጡ ለውድድሩ በተዘጋጀ መተግበሪያ ላይ በቀጥታ በማህበራዊ ሚዲያ ከተሳታፊዎች ጋር ሩጫውን አካሄደዋል።

ተሳታፊዎችም በቤትና ግቢ ውስጥ እንዲሁም የመሮጫ ማሽን ላይ በመሆን እየሮጡ በስልካቸው፣ በኮምፒዩተርና በሌሎች የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በመታገዝ አትሌቶችን እየተከተሉ ሮጠዋል።

በፌስቡክ እና ዩቲዩብ ላይቭ ላይ ከተለያዩ የዓለም ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በተመሳሳይ ሰዓት በአንድ ላይ ሆነው በኢንተኔት በታገዘው ሩጫ ላይ ካሉበት ሆነው ተሳትፈዋል።

ቨርቹዋል ሩጫ (Virtual Race) የሚባለው ከየትኛውም ቦታ እና አካባቢ በመሆን የሚከናወን ሩጫ ወይንም ፈጠን ያለ የእርምጃ ውድድር እንደማለት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም